ፖሊስ በታሰሩ የጤና ባለሙያች ላይ ለምርመራ የጠየቀው የ12 ተጨማሪ ቀን ተፈቀደለት
(መሠረት ሚድያ)- ሰሞኑን የጤና ባለሙያዎች በመላው ኢትዮጵያ እያካሄዱት ካለው የስራ ማቆም አድማ ጋር በተያያዘ በፀጥታ አካላት የተያዙ ባለሙያዎች ዛሬ የፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት መቅረባቸው ታውቋል።
መሠረት ሚድያ የተመለከተው እና ፌደራል ፖሊስ በፅሁፍ ያቀረበው የግዜ ቀጠሮ መጠየቅያ ወረቀት ዘጠኝ ተከሳሾች 'ሁከት እና ብጥብጥብ' ባማነሳሳት ወንጀል እንደተጠረጠሩ ይገልፃል።
"ተጠርጣሪዎቹ ከጥር 2017 ዓ/ም ጀምሮ ሌሎች ካልተያዙ ግብረ-አበሮቻቸው ጋር በመሆን፣ ከፀረ ሰላም ሀይሎች ጋር በመመሳጠር በመደራጀት እንዲሁም እንዲሁም ተልዕኮ በመቀበል በከተማ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ አመፅ እንዲሁም ሁከት እና ብጥብጥ እንዲነሳ ለማድረግ" የሚል ውንጀላ ቁርቦባቸዋል።
ክሱ አክሎም "በሚሰሩበት ስራ ዘርፍ ታካሚዎችን አናክምም፣ አገልግሎት ፈላጊዎችን እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት የስራ ማቆም አድማን ሲቀሰቅሱ" እንደነበር ይጠቅሳል።
ፖሊስ እስካሁን የአካባቢ እና የሰነድ ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን ጠቅሶ ተጨማሪ 12 የምርመራ ቀን የጠየቀ ሲሆን ይህም በፍርድ ቤቱ ተፈቅዶለታል።
ተጨማሪ ቀን ካስፈለገበት ምክንያት አንዱ "ተጠርጣሪዎች ሲሰሩበት በነበረ ሆስፒታል ውስጥ በህክምና መስተጓጎል ህይወታቸው ያለፈ በርካታ ሰዎች ስለመኖራቸው በተገኘ መረጃ መሰረት ይህንን ከተለያዩ ሆስፒታሎች በማስረጃ እከምናረጋግጥ" የሚል ነው።
ላለፉት ሁለት አመታት ስራ ላይ ያልነበረችው እና በቢቢሲ 'Focus on Africa' ፕሮግራም ላይ በመቅረብ የጤና ባለሙያዎቹን ድምፅ ያሰማቸው ዶ/ር ማህሌት ጉዕሽ የታካሚዎች ህይወት ማለፍን በተመለከተ የቀረበው ክስን ስራ ላይ እንዳልነበረች በመጥቀስ ስትከላከል ፖሊስ 'በውጭ ሃገራት ሆነው ከሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ሃይሎች ጋር በመተባበር' የሚል ውንጀላ አቅርቧል።
በዛሬው ዕለት ከዶ/ር ማህሌት በተጨማሪ ተይዘው ፍርድ ቤት የቀረቡት ዶ/ር ሳሙኤል ሀይሉ፣ ዶ/ር ሚኪያስ አለም፣ ዶ/ር ሩት አማረ፣ ዶ/ር ኃይለየሱስ ንጋቱ፣ ሚካኤል ተሰማ፣ ጃፋር አብዱጂላል፣ ኡስማን አዋይ እና አለባቸው ፈቄ ናቸው።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በሕክምና ተቋማት በመካሄድ ላይ ያሉ የሥራ ማቆም አድማዎች ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በር እንዳይከፍቱ ትኩረት ሊሰጣቸው እና ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል ብሏል።
ኢሰመኮ አንዳንድ የሕክምና ባለሙያዎች የደመወዝ እና ከሥራ ሁኔታ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን መንግሥት እንዲመልስ ሰጥተናል ያሉት የ30 ቀናት የጊዜ ገደብ ግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. መጠናቀቁን ተከትሎ በመንግሥት እና በሕክምና ባለሙያዎች በመወሰድ ላይ የሚገኙትን እርምጃዎች በመከታተል እገኛለሁ ብሏል።
መረጃን ከመሠረት!



