ካሜራ የተገጠመላቸው ገቢ ሰብሳቢዎች 11 ሰዓት ላይ ካሜራ ለቢሯቸው ካስረከቡ በኋላ ድጋሜ በመውጣት ዘረፋ ላይ እየተሰማሩ መሆኑ ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- በቪድዮ የታገዘ የግብር አሰባሰብ ሂደት መጀመሩ ይፋ ከሆነ አንድ ወር እንኳን አልሞላውም፣ ይሁንና በዚህ ዙርያ የሚቀርቡ አቤቱታዎች ካሁኑ በስፋት መስተዋል ጀምረዋል።
ከግብር አሰባሰብ ጋር በተያያዘ ከህብረተሰቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመቅረፍ በሚል ተግባራዊ የተደረገው ቴክኖሎጂ ችግሩን እንደሚቀርፍ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የገለፀ ሲሆን በግብር ሰብሳቢ ባለሙያዎች ዩኒፎርሞች ላይ በመግጠም የድምጽና የቪዲዮ መልዕክቶች ለማዕከል ማድረስ የሚያስችል መሆኑ ተነግሮ ነበር።
ቢሮው በድፍረት "ቴክኖሎጂው ሙሉ ለሙሉ ችግሩን ይቀርፋል" ቢልም ገና ካሁኑ አንዳንድ ሰራተኞች የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም እንደጀመሩ መሠረት ሚድያ አረጋግጧል።
ቀን ላይ ካሜራው ስለተገጠመባቸው ህግን አክብረው የሚሰሩት ግብር ሰብሳቢዎቹ ነገር ግን ከ11 ሰዓት በኋላ ካሜራውን ቢሯቸው አስረክበው በድጋሚ ለዘረፋ እንደሚሰማሩ ታውቋል።
“ካሜራ ከመለሱ በኋላ ለምሳሌ የክፍለ ሀገር የጭነት መኪኖች የሚቆሙበት ጋር ይቀመጣሉ። ለሚጫነው እቃ አሰልፈው ደረሰኝ ይጠይቃሉ፣ የተሰጣቸውን ደረሰኝ እንደ መንጃ ፍቃድ ይወስዱትና በደረሰኙ ላይ ባለው አድራሻ ደውለው ደረሱኝን በትክክል አልቆረጥክም ክስ ሊመጣብህ ነው በማለት ከ20 ሺህ እስከ 30 ሺህ ብር እየተቀበሉ ነው። ካልደወሉ ደግሞ በደረሰኙ አድራሻ መሰረት ሱቁ ድረስ እየመጡ ብር ተቀብለው ይሄዳሉ" በማለት አንድ በመርካቶ በንግድ ሙያ ላይ የተሰማሩ ግለሰብ ለሚድያችን አስረድተዋል።
በተመሳሳይ መልኩ ሌላ አንድ በመርካቶ ስራቸውን ያረጉ ግለሰብም "የገቢ ሰብሳቢዎቹ ብዛታቸው ከህዝቡ ቁጥር አይተናነስም፣ መንግስት ህዝቡን ዝረፉ ብሎ ያሰማራቸው ነው የሚመስለው" በማለት ያስረዳሉ።
“ካሜራ ሳይዙ መጥተው እነሱ የሚጠይቁትን ያልተገባ ገንዘብ አልከፍልም እስከ ጥግ እሄዳለው ብትል ሰሚ የለም። ቅጣት 100 ሺህ ይጣልብሃል። 100 ሺው ቅጣት ደግሞ የሚያስከትለው ሌላ ጣጣ አለ። በቅጣቱ ምክንያት ኦዲት ይጠሩሃል፣ እንደገና ደግሞ ኦዲተሮች የኦዲት ግኝት አለብህ በሚል አይተሀው የማታውቀውን ገንዘብ በሚሊየኖች ይጠሩልሃል" በማለት ተናግረዋል።
መሠረት ሚድያ እንዳረጋገጠው ብዙ ግዜ ገቢ ሰብሳቢዎቹ ጉቦ ሲጠይቁ ለምሳሌ "ለእኛ 100 ሺህ ትከፍላለህ ወይስ ለመንግስት 300 ሺህ? ይህ ምርጫ ያቀርባሉ። አንዴ የሚጠሩት ገንዘብ ላይ እንደማይደራደሩ ታውቋል።
"ይሄ የሚሆነው በአነስተኛው ነጋዴ ላይ ነው፣ ትልልቅ ነጋዴዎችን ምን እንደሚያደርጓቸው ፈጣሪ ይወቀው። እኔ በጣም አስጠልቶኛል፣ ግድ ሆኖብኝ እንጂ እዚያ ስራ ቦታ ባልሄድ ከራስ ምታትና ጭንቀት እድናለው" በማለት አንድ ነጋዴ ይናገራሉ።
"ሱቁ ከተከፈተ በኋላ ዘግተን እስክንወጣ ከባድ ውጥረት ነው ያለው። ሰዎች ከሌላ ቦታ ይዘውት የመጡትን ፌስታል ወደ ሱቅ ይዘውብኝ እንዳይገቡ ደጅ ላይ እጠብቃለው" በማለት ይናገራሉ።
ይህን ሲያስረዱም "ከሌላ ቦታ ይዘውት የመጡትን ፌስታል ይዘውት ገብተው እሱንው ይዘውት ሲወጡ የገቢዎች ሰራተኞች ደረሱ ማለት ከ20 ሺህ እስከ 30 ሺህ ብር ያስተፉሃል። ሰዎች ይዘውት የገቡት እቃ እዚያ ሱቅ ላይ የማይሸጥ እቃ እንኳን ቢሆን አይሰሙህም" ብለዋል።
"በገዛ ሀገራችን እንደ ሌላ ሀገር ዜጋ፣ ሀገሩን ለቆ እንዲወጣ እንደተፈለገ ስደተኛ እየተቆጠርን ነው" በማለት መንግስት በአስቸኳይ ይህን ካሜራ ከተመለሰ በኋላ የሚፈፀም አዲስ ውንብድና እንዲያስቆምላቸው ጠይቀዋል።
-መሠረት ሚድያ-




100% የትባለው ነገር ሁሉ ልክ ነው ግን የንጋዴውን ጩህት ሚሰማ የለም
ምን ጉድ ናቸው 🤔