(መሠረት ሚድያ)- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ቡልዲግሉ ወረዳ ዳለቲ ቀበሌ በታጣቂዎች በተሰነዘረ ድንገተኛ ጥቃት የሟቾች ቁጥር ከ105 በላይ ማለፉ ተገለጸ።
በጥቃቱ ንጹሐን ዜጎች፣ ወጣቶች፣ ሕፃናት እንዲሁም የክልሉ ልዩ ኃይል አድማ ብተና፣ የፖሊስና የሚሊሻ አባላት ሰለባ ሆነዋል።
ጥቃቱ ጥቅምት 26 ቀን ንጋት አካባቢ በታጣቂዎች ድንገተኛ ተኩስ የተከፈተ መሆኑን አንድ ክልሉ መንግስት ባለስልጣን ስሜ አይጠቀስ በማለት ለሚድያችን የተናገሩ ሲሆን ጥቃቱን የፈጸመው "ኦነግ ሸኔ" የተባለው አካል እንደሆነ ተናግረዋል።
ጥቃቱ በደረሰበት ወቅት በአካባቢው የመንግስት የጸጥታ አካላት የነበሩ ቢሆንም ጥቃቱ ሊደርስና ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል የቻለው በጸጥታ ኃይሎች በኩል በነበረ ከፍተኛ መዘናጋትና አስቀድሞ ለደረሱ የደህንነት መረጃዎች ትኩረት አለመስጠት እንደሆነ ተገልጻል። ሆን ተብሎ የሸኔዎች እንቅስቃሴ እንዳይታወቅ ተደርጓል የሚል ወሬ እንዳለ ጠቅሰው በዚህ ዙርያ የክልሉ መንግስት ማጣራት እንደጀመረ አስረድተዋል።
ከግድያው ባሻገር ታጣቂዎቹ በዳለቲ ቀበሌ በሚገኙ የንግድ ሱቆችና ንብረቶች ላይ ሰፊ ዘረፋ መፈፀማቸው ታውቋል።
"በጥቃቱ የቆሰሉ በርካታ ንጹሐን ዜጎችና የጸጥታ አባላት በአቅራቢያ በሚገኙ የሕክምና ተቋማት እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል። በአሁኑ ወቅት የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በታጣቂዎቹ ላይ የአጸፋ እርምጃ እንደወሰዱ እየሰማን እንገኛለን" ያሉት ደግሞ አንድ የሆስፒታል ምንጭ ናቸው።
"አብዛኞቹ በጥይት የተመቱ፣ ጥቂቶች ደግሞ በስለት ተወግተው ህይወታቸው አልፏል፣ የቆሰሉም በርካቶች ናቸው። በክልሉ እንዲህ አይነት ክስተት አዲስ ባይሆንም በዚህ መጠን ሰው ተጎድቶ አይቼ አላውቅም" በማለት እኚህ የጤና ባለሙያ የሆኑ ምንጭ ይናገራሉ።
"ዛሬ ብቻ አይደለም፣ ምስኪኑ ህዝብ በኦነግ ሻኔ የጅምላ ጭፍጨፋ በተደጋጋሚ እየተደረገበት ነው ያለው፣ ግን የሚገርመው ነገር ቢኖር መንግስት ዝምታ መምረጡ ነው" ብለው አስተያየታቸውን የሰጡት አንድ የአካባቢው ነዋሪ ናቸው።
በዚህ ዙርያ ተጨማሪ መረጃዎችን እያሰባሰብን እንገኛለን።
| መሠረት ሚድያ |



ብልፅግና በጫካ ያስቀመጠው
በወንበዴ ጦር የተፈፀመ
የጂምላ ጭፍጨፋ ነው
አሳፋሪ ዘመን ነው ፣ እነዚሀን ሰዎች መንግስት ናቸው ማለት ይቻላል ?? በየአቅጣጫው እንደ ሰደድ እሳት ጦርነት እያቀጣጠሉ ነዲዱን ሙሞቅ ምነ ይሉታል ? ሀይ ባይ የጠፋበት ፣ ሆድ አደር የተትረፈረፈበት አስቸጋሪ ዘመን ።