በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ ውስጥ በተከሰተው የመሬት ናዳ ህይወታቸው ያለፈ ዜጎች ቁጥር 102 ደረሰ
(መሠረት ሚድያ)- ከሰሞኑ በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ ማዞ ዶይሻ ቀበሌ በደረሰ ድንገተኛ አደጋ የ102 ወገኖቻችን ህይወት ማለፉን እንዲሁም እስካሁን የ52 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን የዞኑ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ዛሬ አስታውቋል።
በስፍራው ዛሬ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል፣ ይሁንና በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አሁን ላይ መጠለያቸው ፈርሶ ከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸው እየተነገረ ነው።
በቀጣይ መሰል አደጋ እንዳይደርስ በቅንጅት እንደሚሰራ የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን በመደገፍ ወደ ቀደመ ኑሯቸው እንዲመለሱ የማድረግ ስራ በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ወ/ሮ አምፀሐይ ጳውሎስና እና የፌደራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማሪያም በበኩላቸው በደረሰው ጉዳት እጅግ ማዘናቸውን ገልፀው የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ተጨማሪ ጉዳት እንዳይከሰት ህብረተሰቡ አስፈላጊ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በመሬት መንሸራተት አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ወገኖች ቤተሰቦችን ባፅናኑበት ወቅት አሳስበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመሬት መንሸራተትና በጎርፍ ምክንያት የተከሰተውን አደጋ አስመልክቶ ፈጣን ምላሽ መስጠት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከጋሞ ዞን እና አርባ ምንጭ ከተማ አመራሮች ጋር መወያየታቸው ተሰምቷል።
በጋሞ ዞን በደረሰው ድንገተኛ አደጋ የተጎዱ ወገኖቻችንን ለመደገፍና የተደቀነውን ስጋት በጋራ ለመወጣት የገቢ ማሰባሰቢያ ጥሪ ተጀምሯል።
በአቅምዎ በሚከተሉት የባንክ አካውንቶች ድጋፍዎን ማድረግ ይችላሉ:
📌 የጋሞ ልማት ማህበር (CBE)
💳 አካውንት ቁጥር፦ 1000021467174
📌 የጋሞ ዞን አደጋ ስጋት (CBE)
💳 አካውንት ቁጥር፦ 1000321312865
-መሠረት ሚድያ-



