የግራንድ አፍሪካ ራን አዘጋጆች 'ከሩጫም በላይ ነው!' በሚል መርሃ ግብር 10 የበጎ አድራጎት አጋሮችን አስተዋወቁ
(መሠረት ሚድያ)- የግራንድ አፍሪካ ራን አዘጋጆች በዋሽንግተን ዲሲ ባካሄዱት ጋዜጣዊ መግለጫ በዘንድሮው ዝግጅት አብረዋቸው የሚሠሩ 10 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን በይፋ አስተዋውቀዋል።
" ከሩጫም በላይ ነው!" በሚለው መርሃ ግብር አዘጋጅ አካሉ በኢትዮጵያ፣ በአሜሪካና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ድጋፍ የሚሹ ማኅበረሰቦችን ከሚያገለግሉ ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ ገልጻል።
እነዚህ አጋር ድርጅቶች በካንሰር ግንዛቤና ሕሙማን ድጋፍ፣ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ወገኖች በማገዝ፣ የሕፃናት ትምህርትን በመደገፍ፣ ድህነትን በመቀነስ፣ የነርሶችና የሌሎች ባለሙያዎችን አቅም በማጎልበት እንዲሁም ንጹሕ የመጠጥ ውኃ በማቅረብ ዘርፍ የተሰማሩ ናቸው።
በጋዜጣዊ መግለጫው የተወከሉት የየተቋማቱ ተወካዮች ማኅበረሰቡ በዝግጅቱ እንዲሳተፍ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ተሳታፊዎችም የመረጡትን የበጎ አድራጎት ድርጅት በመደገፍ ተሳትፏቸውን ትርጉም ያለው እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በምዕራቡ ዓለም የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሩጫ ዝግጅቶችን ለገቢ ማሰባሰቢያነት ይጠቀሙበታል። በተመሳሳይ መልኩ እነዚህ 10 ድርጅቶች ግራንድ አፍሪካ ራንን እንደ መድረክ በመጠቀም ተሳታፊዎች ከወዳጅ ዘመዶቻቸውና ከሥራ ባልደረቦቻቸው ገቢ እንዲያሰባስቡ ዕድል ያመቻቻሉ።
ተሳታፊዎች የአምስት ኪሎ ሜትር ርቀቱን በመክፈል ወዳጆቻቸው ለእያንዳንዱ ርቀት ድጋፍ እንዲያደርጉ በኢሜይል፣ በአጭር ጽሑፍ፣ በስልክ ወይም በማኅበራዊ ሚዲያ መጠየቅ ይችላሉ ተብሏል።
የሚሰበሰበው ገቢ በቀጥታ ወደ ተመረጠው ድርጅት እንደሚገባ የተጠቀሰ ሲሆን ተሳታፊዎችም በድረ ገጹ ላይ የተሰበሰበውን መጠንና የደጋፊዎችን ማንነት መከታተል ይችላሉ።
የኖቫ ኮኔክሽንስ፣ የዝግጅቱ ዳይሬክተር ዶክተር ጋሻው አብዛ እንደገለጹት ይህ መርሃ ግብር የማኅበረሰብ ግንኙነትን ከማጠናከሩም በላይ እያንዳንዱ እርምጃ ለበጎ ዓላማ እንዲውል መንገድ ይከፍታል።
በተጨማሪም የዘንድሮው 8ኛው ግራንድ አፍሪካ ራን ልዩ ገጽታ በአሌክሳንድሪያ ቶዮታ ስፖንሰርነት የቀረበው የ2026 ሞዴል ቶዮታ ኮሮላ የመኪና ዕጣ ሽልማት ነው።
"ለሽልማቱ ብቁ ለመሆን ፈጣን ሯጭ መሆን አያስፈልግም፤ ለተመዘገቡ ተሳታፊዎች ሁሉ እኩል ዕድል የሚሰጥ ሲሆን አሸናፊው በመዝጊያ ፕሮግራሙ ላይ ይፋ ይደረጋል" በማለት ይፋ ተደርጓል።
8ኛው ዓመታዊ ግራንድ አፍሪካ ራን ቅዳሜ፣ ጥቅምት 10 ቀን 2026፣ በአሌክሳንድሪያ፣ ቨርጂኒያ "አብሮነት መሻል ነው!" በሚል መርህ ይካሄዳል።
የዘንድሮው 10 የበጎ አድራጎት አጋር ድርጅቶች Alpha Breast Cancer Support Service (ABCSS), The Belisha Foundation, Wegene Ethiopian Foundation (WEF), Ethiopian Eritrean Special Needs Community (EESNC), CARE For Ethiopia, Your Ethiopian Professionals Network (YEP), Ethiopian Nurses Association in North America (ENANA), WIHA, Raeye Children Aid (RCA), እና African Women’s Cancer Awareness Association (AWCAA) ናቸው።
| መሠረት ሚድያ |


