በምርጫው ከድሬዳዋ እጪ በመሆን ቀርቦ የነበረው ዶ/ር ሀብታሙ ዓለሙ 1 ሜትር በ 80 ሴንቲሜትር በሆነ ክፍል ውስጥ ታስሮ እንደሚገኝ ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- በድሬዳዋ-1 የምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በግል እጩነት ቀርቦ የነበረውና ከሁለት ሳምንት በፊት ለስራ ወደ ሆስፒታል ሲጓዝ በቁጥጥር ስር የዋለው ዶክተር ሀብታሙ ዓለሙ በአሁኑ ወቅት ሰብአዊነት በጎደለው እና እጅግ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ታስሮ እንደሚገኝ የደረሰን መረጃ ያመላክታል።
ለሚዲያችን በደረሰው ወቅታዊ መረጃ መሠረት ዶክተር ሀብታሙ ዓለሙ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻውን ለአንድ ሰው ብቻ በተዘጋጀ እጅግ ጠባብ ክፍል ውስጥ ታስሮ ይገኛል።
የክፍሏ ስፋት 1 ሜትር በ 80 ሴንቲሜትር ብቻ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን ይህ ዓይነቱ የእስር አያያዝ በእሱ ላይ ቀጣይነት ያለው የስነ-ልቦና ስብራት (Psychological breakdown) ለማድረስ ሆን ተብሎ የታለመ ሙከራ ሳይሆን እንዳልቀረ የቅርብ ምንጮች ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ከሁኔታው አሰቃቂነት የተነሳ ዶክተር ሀብታሙ ወደ መጸዳጃ ቤት እንኳ ወጥቶ መጠቀም እንዳይችል የተከለከለ መሆኑም ታውቋል።
ይህ የተፈጸመው ድርጊት እጅግ ልብ የሚሰብርና ሰብአዊ መብትን በከፍተኛ ደረጃ የጣሰ መሆኑን የገለጹት ምንጮች ጉዳዩን ለመመልከት ለሐምሌ 3 ቀን የፍርድ ቤት ቀጠሮ እንደተሰጠውም አስታውቀዋል።
ከእስሩ ጀርባ ያለው የፖለቲካ ዳራ
ዶክተር ሀብታሙ ዓለሙ ሸዋ ሰኔ 9 ቀን 2018 ዓ.ም ጠዋት ወደ ሥራ ቦታቸው በመጓዝ ላይ እያለ በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋሉ ይታወሳል።
የጸጥታ አካላት ዶክተር ሀብታሙን በቁጥጥር ስር ካዋሉ በኋላ በመኖሪያ ቤቱ ላይ ድንገተኛ ፍተሻ ያካሄዱ ሲሆን ለምርመራ ያግዛሉ የተባሉ ላፕቶፕ ኮምፒውተሮችን እና ሌሎች የግል የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን መውሰዳቸውን የዓይን እማኞች በወቅቱ መግለጻቸው ይታወሳል።
የታዛቢዎች አስተያየት
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዶክተር ሀብታሙ ዓለሙ መታሰርና አሁን እየተፈጸመበት ያለው አስከፊ እንግልት ቀደም ሲል በድሬዳዋ ከተማ ከነበረው ውጥረት የነገሠበት የፖለቲካ ምሕዳር ጋር የተያያዘ መሆኑን የቅርብ ታዛቢዎች ይናገራሉ።
ዶክተር ሀብታሙ በወቅቱ በግል እጩነት በነበረበት ወቅት የድሬዳዋ የጸጥታና ፍትህ አካላት የሕግ ጥሰት እየፈጸሙ ነው በሚል እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለአቤቱታቸው ተገቢውን ምላሽ አልሰጠም በማለት ከምርጫው ራሳቸውን በይፋ ማግለሉ ይታወሳል።
በወቅቱ በሰጠው መግለጫ ደጋፊዎቹ እና ጓደኞቹ ሆን ተብሎ እንዲታሰሩ መደረጉን፣ ዋስትና መከልከላቸውን እና ሕዝቡ እሳቸውን እንዳይደግፍ የማስፈራራት ሥራ መሠራቱን አጋልጦ የነበረ ሲሆን አሁን የተፈጸመው እስር እና የሰብአዊ መብት አያያዝ ጥሰት የዚሁ ቀጣይነት ያለው የፖለቲካ ጫና አካል ሳይሆን እንዳልቀረ በሰፊው እየተነገረ ይገኛል።
| መሠረት ሚድያ |


