"ከአርብ ዕለት ጀምሮ ቢሮዎቻችን ታሽገው ወደቤታችሁ ተመለሱ ተብለናል"- በአዲስ አበባ ያሉ የመንግስት ሰራተኞች
(መሠረት ሚድያ)- ሚድያችን ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በተከታታይ ለህዝብ ባቀረባቸው ዘገባዎቹ ከሀምሌ 1/2017 ዓ.ም ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ የመንግስት ሰራተኞች ከስራቸው መሰናበት እንደሚጀምሩ ሲጠቁም ነበር።
ይህን ተከትሎ ለመንግስት ሚድያዎች ሰኔ ወር ላይ ምላሽ የሰጡት የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር መኩሪያ ኃይሌ 'በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች' ሠራተኞች ይቀነሳሉ በሚል የሚናፈሰው መረጃ ትክክል እንዳልሆነ ደጋግመው ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ይሁንና ዶ/ር መኩሪያ ከዚህ ቀደም የሰጡትን የ 'ሰራተኛ አይቀነስም' መግለጫ በሚጣረስ መልኩ ለመንግስት ሚድያዎች ሀምሌ 1 ቀን በሰጡት መግለጫ መንግስት ከሀምሌ 1 ጀምሮ የሽግግር ምዕራፍ አጠናቆ ወደ ትግበራ ምዕራፍ እንደሚሻገር ገልፀዋል።
አሁን ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ በርካታ ወረዳዎች ውስጥ ሲሰሩ የቆዩ የመንግስት ሰራተኞች ከአርብ ጀምሮ ቢሯቸው ታሽጎ 'ወደቤታችሁ ተመለሱ ተብለናል' ብለው ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል።
"በወረዳ ደረጃ ያሉ እንደ መሬት አስተዳደር፣ ግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር፣ ቤቶች አስተዳደር፣ ባህል እና ኪነ ጥበብ ወዘተ ያሉ ተቋማት ሰራተኞች ቢሯቸው ታሽጎባቸዋል። የሰራተኛ ቅነሳ እንዳለ በወሬ ደረጃ ስንሰማ ብንቆይም በዚህ ፍጥነት እና በአንዴ ይሆናል ብለን አልገመትንም" በማለት አንድ ስሜ አይጠቀስ ያለ የከተማ አስተዳደሩ ሰራተኛ ተናግሯል።
"ቅዳሜ ቢሮ ስንገባ ቢሮው ታሽጎ አገኘነው። ምንድነው ስንል ደብዳቤ ይደርሳችሗል ተባልን። በዚህ ስራ በጠፋበት እና ኑሮ በተወደደበት ወቅት ምን አርገን ቤተሰብ ልናስተዳድር ነው? ዛሬ ሰኞም ቢሮ ሄደን ግቢ ውስጥ ውለን ነው የመጣነው፣ ቢሮው እንደታሸገ ነው" በማለት ለመሠረት ሚድያ የተናገሩት ደግሞ አንድ የቤቶች አስተዳደር ፅህፈት ቤት ሰራተኛ ናቸው።
ሚድያችን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ተፅፎ የተፈረመ እና ማህበራዊ ሚድያ ላይ እየተዘዋወረ የሚገኝ አንድ ደብዳቤን የተመለከተ ሲሆን ደብዳቤው ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጧል።
ይህ ደብዳቤ የክፍለ ከተማ እና የወረዳ አደረጃጀት ማሻሻያን የተመለከተ ሲሆን በክፍለ ከተማ ደረጃ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ፅህፈት ቤት ታጥፎ በቡድን ደረጃ እንዲደራጅ ያዛል።
በተመሳሳይ በወረዳ ደረጃ የስራ አስኪያጅ ፅ/ቤት፣ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ወዘተ ታጥፈው በክፍለ ከተማ ደረጃ እንዲከናወኑ እንደሚደረግ ይጠቁማል።
ሚድያችን በዚህ ዙርያ ባደረገው ክትትል አዲሱን የሰራተኛ አዋጅ ተከትሎ ከወዲሁ ሌሎች በርካታ የመንግስት ተቋማትም ለሰራተኞቻቸው ከስራቸው እንደሚሰናበቱ እያሳወቁ ይገኛሉ። አዋጁ ዋና አላማው "ተቋማት ተልዕኳቸውን በብቃት እንዲፈፅሙ የሚያስችል ነው" የሚል ነበር።
ለምሳሌ በኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ከሀምሌ 1 ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ብቻ 350 ነባር ሰራተኞች ከስራቸው እንደሚቀነሱ ተነግሯቸዋል። አብዛኞቹ ተቀናሾች በተቋሙ ከ15 እስከ 20 አመት ያገለገሉ ነባር ሰራተኞች መሆናቸው ታውቋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በአዋጁ አላማና አስፈላጊነት ዙሪያ የዛሬ አራት ወር ገደማ ማብራሪያ ሰጥተው በነበሩበት ወቅት በመንግስት አቅጣጫ ከተያዘባቸው ጉዳዮች አንዱ "ከሚያስፈልገው በላይ የመንግስት ሰራተኛ አለ" የሚለው ዋናው መሆኑን ጠቅሰው ነበር።
ዶ/ር ነገሪ አክለውም "የመንግሥት ሠራተኞች የብዛታቸውን ያህል የሚሠሩት አገልግሎት የሚያረካ አይደለም፣ የተወሰኑ ይሠራሉ፤ ሌሎቹ ግን የተወሰኑ ሠራተኞች በሠሩት ትከሻ ላይ ተንጠላጥለው ይኖራሉ" በማለት ኮሚሽነር መኩሪያ ሀይሌ ከተናገሩት ጋር የሚቃረን መረጃ ከህዝብ ሰጥተው ነበር።
መረጃን ከመሠረት!




