ለጤና ባለሙያዎች እና መምህራን ከወራት በፊት ቃል የተገባው ጉዳይ ምን ላይ ደረሰ?
(መሠረት ሚድያ)- ከጥቂት ወራት በፊት በሀገር አቀፍ ደረጃ በጤና ባለሙያዎች ተከናውኖ የነበረውን የስራ ማቆም አድማ ተከትሎ መንግስት ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ባደረገው በርካታ ውይይቶች ቃል የተገቡ እና ስምምነት የተደረሰባቸው ብዙ ጉዳዮች ነበሩ።
የጤና ሚኒስቴር አመራሮች እና ጠ/ሚር አብይ አህመድ በመሯቸው ሁለት የተለያዩ ስብሰባዎች ላይ 'አቅም በፈቀደ መጠን' የጤና ባለሙያዎችን ጥያቄዎች በአጭር ግዜ በመፍታት መፍትሄ እንደሚሰጣቸው ተደጋግሞ ሲነገር ቆይቷል።
በተመሳሳይ ከሁለት ወር በፊት ከመምህራን ጋር በተደረጉ ውይይቶች ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን መንግስት በየደረጃው ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረው ነበር፣ አንዱ መፍትሄ ደግሞ የመምህራንን የመኖርያ ቤት ጥያቄ በሂደት ለመፍታት በማህበራት ተደራጅተው ቁጠባ እንዲጀምሩ ማረግ ነበር።
ይሁንና እነዚህ ቃል የተገቡ ጉዳዮች ላይ አንዳንድ መንሸራተቶች እንዳሉ ከሰሞኑ ያሰባሰብናቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
የስራ ማቆም አድማው ላይ ተቀላቅለው ከነበሩት የህክምና ባለሙያዎች መሀል የጥቁር አንበሳ ኢንተርን ሀኪሞች ይገኙበት ነበር፣ ንቁ ተሳትፎም ሲያደርጉ ታይተው ነበር።
ይህን ተከትሎ የስራ ማቆም አድማው ከቆመ እና ከአስተዳደር አካላት ጋር በመነጋገር ደሞዛቸው እንደማይቋረጥ ተነግሯቸው የነበሩት እነዚህ ኢንተርን ሀኪሞች አሁን ላይ 'ደሞዝ ብላችሁ ከዚህ በኋላ እንዳትጠይቁ' መባላቸውን ለመሠረት ሚድያ ጠቁመዋል።
"በአድማው ግዜ የተሳተፍነው እንደ ሀገር ነው፣ ከዛ በኋላ በነበረን ንግግር ወቅት ክፍያችን እንደማይቆም ተናግረው የነበሩ ቢሆንም አሁን ከልክለውናል" በማለት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የጤና ባለሙያዎ ተናግረዋል።
"ከአስተዳደር አካላት ጋር ሰብስበውን አውርተን ደሞዛችን እንደማይቋረጥ እና ሌሎች ጥያቄዎችንም እንደሚመልሱልን ተስማምን ነበር የተመለስነው። ይሁንና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ለኢንተርኖች ደሞዝ ሳያስተጓጉሉ ተከፍሏቸው ቀጥለዋል። እኛን ግን በተደጋጋሚ ስንጠይቅ 'እንከፍላችኋለን' ሲሉ ቢቆዩም አሁን ላይ 'ሁለተኛ እንዳጠይቁን የሚል ዛቻ እያደረሱብን ነው'" በማለት ተናግረዋል።
ሌላ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሚሰራ ሜዲካል ዶክተር ደግሞ ከአድማው በፊት ክፍያቸው በሶስት እና አራት ወር ይዘገይ እንደነበር ይናገራል።
"አሁን ጭራሽ አንከፍልም ነው የሚሉት፣ ልክ እንደ ወንጀለኝን አድርጎ የማየት ሁኔታ ነው ያለው" በማለት አስረድተዋል።
አክለውም "የመጀመሪያው ስብሰባ ሰኔ 2/2017 ዓ.ም ነበር። ጥያቄዎችን እንደሚመልሱ፣ ደሞዝም ተመድቦ ቁጭ ያለ ነው ይሰጣችኋል ተብለን ነበር። ይህን ቃላቸውን ይዘን ስራ ጀመርን፣ ከዛ ግን ተደጋጋሚ ጠየቅን፣ ምላሽ ስንጠብቅ ይባስ ማስፈራርያ እየደረሰን ነው" በማለት ተናግረዋል።
በመምህራን ዘንድም በተመሳሳይ ወደኋላ የማለት ሁኔታ እንዳለ ታውቋል።
ለምሳሌ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ ከአንድ ወር ተኩል በፊት ከመምህራን ጋር በነበራቸው ስብሰባ ላይ መምህራን ሲጠይቁ የነበረው ዋናው ጉዳይ ቤት ነበር።
የከተማ አስተዳደሩ የመስሪያ ቦታ በማዘጋጀት እና 120 ቢሊዮን ብር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር በማመቻቸት ስራው እንደሚሰራ ተጠቅሶ ነበር።
"በወቅቱ ከእናንተ የሚጠበቀው መደራጀት ነው። 25 ፐርሰንት በ3 አመት ቆጥባችሁ ቤቱን ስትረከቡ 75 ፐርሰንቱን መክፈል ትጀምራላችሁ ተብሎ ነበር፣ መክፈል ለማይችሉ የኪራይ ቤት ይዘጋጃል ተብሎም ነበር" በማለት ለሚድያችን የተናገሩት አንድ መምህር ናቸው።
በዚህ ስብሰባ ላይ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ እና የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ሀላፊ ተገኝተው ነበር።
ከዛ በኋላ ግን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሀላፊው ዶ/ር ዘላለም ሐምሌ 9 እና 10 ቀን አጠቃላይ ስልጠና እና ግምገማ ብለው የትምህርት አመራሮችን ሰብስበው ሌላ ጉዳይ እንዳመጡ ታውቋል።
"የቤቱ ጉዳይ ሲጠየቅ ቤቱ የሚገነባው እናንተም የምትደራጁት ዛሬ እና ነገ 25 ፐርሰንት ቅድመ ክፍያ ስትከፍሉ ነው ብሎ አረፈው፣ ያልከፈለ የሚደራጀው እየቆጠበ ኖሮ 25 ፐርሰንት ሲሞላለት ነው ተብሏል፣ ይህን ቀድመን ያልተነጋገርንበትን አዲስ ሀሳብ ይዞ መጥቷል" ብለው ይናገራሉ።
ሌላኛ መምህር ደግሞ "ያ ሲለፋበት የኖረው እና ከተማ አስተዳደሩ የወሰነው ትልቅ ውሳኔ በዚህ መልኩ ተጠናቋል። የእኛ ጥያቄ 120 ቢሊዮን ብሩ ለማን ነው የተፈቀደው የከንቲባዋ ውሳኔ ለምን በትምህርት ቢሮው ተሻረ? የመምህራን ማህበሩ የተገባልን ቃል ይሄ አይደለም ማለት ለምን ከበደው? አስቸኳይ ገንዘብ አስገቡ የሚለው ግርግር ከየት መጣ?" የሚሉ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል።
"መምህር የሚረሳ አይመስለኝም ነበር፣ እኔ ግን አልረሳውም… ወ/ሮ አዳነች አበቤ እኛ አልረሳነውም። የረሱት የትምህርት ቢሮ ሀላፊው እና የመምህራን ማህበር ሀላፊ ተብየው ናቸው" በማለት ተናግረዋል።
በዚህ ዙርያ ከጤና ሚኒስቴር እና ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምላሽ ለማግኘት ያረግነው ሙከራ አልተሳካም።
መሠረት ሚድያ!



