“ጉዳያችን እየታየ ያለው በፍርድ ቤት ሳይሆን በፖለቲከኞች ጠረጴዛ በመሆኑ ከእንግዲህ ፍርድ ቤት አንቀርብም"- የፖለቲካ እስረኞች
(መሠረት ሚድያ)- በእነ ዶክተር ወንደሰን አሰፋ፣ መስከረም አበራ፣ ጎበዜ ሲሳይ፣ ዳዊት በጋሻው እና ገነት አስማማው መዝገብ ስር የሚገኙ አስራ ስድስት ተከሳሾች ለፍርድ ቤት በላኩት አዲስ አቤቱታ "የብልፅግና መንግሥት ባለስልጣናት በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ በግልፅ እጃቸውን በማስገባት ለሞት ቅጣት እያዘጋጁን ነው” ማለታቸውን ሚድያችን ሰምቷል።
ተከሳሾቹ በዚህ አቤቱታቸው ላይ እንዳሉት “ዓቃቤ ሕግ ያለምንም ማስረጃ ክስ መስርቶብን ሳለ ይሄንኑ እንድንከላከል መብታችንን ስንጠይቅ 'ፍርድ ቤት ሳትቀርቡ ከማረሚያ ቤት ሆናችሁ በፕላዝማ ተከላከሉ' መባሉ በኢትዮጵያ የፍትሕ ታሪክ ውስጥ ተደርጎ የማያውቅ ብይን በእኛ ላይ እንዲፈፀም ተፅዕኖ እየተደረገ ያለው በፖለቲከኞች ግፊት ነው" ብለዋል።
አክለውም "የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሕገ-መንግስት እና የፀረ-ሽብር አንደኛ ወንጀል ችሎት በሞት በሚያስቀጣ ወንጀል ተከላከሉ ብሎ ከበየነ በኋላ ፍርድ ቤት ሳንቀርብ እንዴት ነፍስን የሚያስቀጥፍ የወንጀል ክስን መከላከል ይቻላል? የሚለውን ጥያቄ መልስ አጥቶት ሳይሆን ተገዶ መሆኑን ያሳያል" ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአገሪቱ የፍትሕ ማስፈፀሚያ ቁንጮ የሆነው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከላከሉ ብሎ የበየነብንን ፍሬ ጉዳይ በወረቀት ገልብጦ መስጠት ሲገባው በጀት አልቆብኛል ሲል በግልፅ ከልክሎናል በማለት የፖለቲካ እስረኞቹ ተናግረዋል።
"ይህ የሚያሳየው ተፈፀመ የተባለውን ወንጀል በግልፅ ቀርበን እንዳንከላከል እና ባለስልጣናት በእኛ ላይ እንዲፈፀም የሚፈልጉት የሞት ፍርድ በቶሎ እንዲጠናቀቅላቸው ነው" ሲሉም አመልክተዋል።
ተከሳሾቹ ጨምረው እንዳሉት "በግልፅ ችሎት ቀርበን በውሸት የተመሰረተብንን ክስ እና ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ማስረጃ ውድቅ እንደምናደርገው ከወዲሁ ቀድሞ ግምት ስለተወሰደ ዓቃቤ ሕግ በችሎት ቀርቦ ምስክሮቻችንን ሲጠይቅ እኛ ደግሞ ማረሚያ ቤት ሆነን በፕላዝማ እንድንጠይቅ መደረጉ እና በየትኛው ማስረጃ ላይ መከላከል እንዳለብን የሚገልፅ የብይኑ ግልባጭ ሳይደርሰን መከራከር ስለማንችል ብሎም ፍርድ ቤቱ የገዢው መንግስት ፍላጎት እያስፈፀመ በመሆኑ ከእንግዲህ ፍርድ ቤት በአካልም ሆነ በፕላዝማ ላለመቅረብ ወስነናል" ብለው ማመልከታቸውን የመሠረት ሚዲያ የፍርድ ቤት ምንጮች ጠቁመዋል።
ከሦስት ዓመታት በፊት በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በማረሚያ ቤት የሚገኙት በእነ ዶክተር ወንደሰን አሰፋ መዝገብ ዶክተር ሲሳይ አውግቼው፣ ዶክተር ግብረዓብ አለሙ፣ ዶክተር መሰረት ቀለመወርቅ እና ጠበቃ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አለልኝ ምህረቱ ይገኙበታል።
| መሠረት ሚድያ |


