በኮሪደር ልማት ከካዛንችስ ወደ ቃሊቲ ወርቁ ሰፈር የተወሰዱ ዜጎችን ምን ገጠማቸው?
(መሠረት ሚድያ)- በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ባለው ሰፊ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ምክንያት ከአርባ ዓመታት በላይ ከኖሩበት የታሪክና የማህበራዊ ትስስር ማዕከል ከነበረው ካዛንችስ አካባቢ በአንድ ቀን አጭር ማስጠንቀቂያ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ያሉበትን ሁኔታ መሠረት ሚድያ ቃኝቷል።
በቃሊቲ ወርቁ ሰፈር በሚገኙ 5 ሺህ ተገጣጣሚ ቤቶች ውስጥ በከባድ እንግልት፣ መከራና የሰብዓዊ መብት መጣስ ውስጥ እንደሚገኙ ነዋሪዎቹ እየገለፁ ይገኛሉ።
ነዋሪዎቹ ለአዲሱ የመልሶ ማቋቋሚያ ቦታ የተመደበው በጀት 'በሙስና' መበላቱን እና መሠረታዊ ፍላጎቶች እንኳ እንዳልተሟሉላቸው በመግለጽ ይናገራሉ።
"አዲሶቹን ተገጣጣሚ ቤቶች የመገንባት ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ECWC) እና ንዑስ ተቋራጮች መንግሥት ክፍያ አልፈጸመልንም በሚል ምክንያት እጅግ ጥራት የጎደለውና በፊታችን የሚፈርስ ሥራ ሠርተው ወጥተዋል" የሚሉት አንድ የልማት ተነሺ አዛውንት ናቸው።
የ72 አመት ባለፀጋው አክለውም ቤቶቹ ገና ከመግባታቸው ዝናብ የሚያስገቡ፣ የመብራትና የውሃ ዝርጋታቸው ያልተጠናቀቀ እና ለሰው ልጅ መኖሪያነት በጭራሽ የማይመጥኑ ናቸው። ነዋሪዎች የዝናብ ውሃ በቤታቸው ውስጥ በባልዲ እየቀዱ ለመኖር መገደዳቸውን በቁጭት ይናገራሉ።
ከቤት ጥራት መጓደል በተጨማሪ የአካባቢው የመሠረተ ልማት ችግር ሌላው አስከፊ ፈተና ሆኖባቸዋል።
"ወደ ሰፈሩ የሚያስገባው መንገድ ሙሉ በሙሉ በመበላሸቱና በጭቃ በመሸፈኑ ምክንያት ተሽከርካሪዎች የሚሰበሩበት፣ ህጻናትና አረጋውያንን ጨምሮ ነዋሪዎች ወጥተው መግባት የማይችሉበት አሰቃቂ ሁኔታ ተፈጥሯል" የሚሉት ሌላው የቀድሞ የካዛንችስ ቀደምት ነዋሪ ናቸው።
ይህንኑ ምሬትና እንግልት ለክፍለ ከተማው አመራሮች ያቀረቡት ነዋሪዎች ለችግራቸው አፋጣኝ መፍትሔ ከማግኘት ይልቅ "ለልማት ተባባሪ አይደላችሁም" የሚል ውንጀላ እና "ከንቲባዋ ቤቶቹን ልትመርቅ ስትመጣ ይሰራላችኋል" የሚል የፌዝ ምላሽ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ቤቶች ተሰርተው እስኪያልቁ ድረስ በዚህ አሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ እንዴት መቆየት እንደሚችሉ ግራ መጋባታቸውን ገልፀዋል።
በአዲስ አበባ የሚካሄደው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር የተወጠነ ቢሆንም እንደ ካዛንችስ ያሉ ነዋሪዎች ያለበቂ ካሳና ዝግጅት ወደ ከተማዋ ዳርቻዎች መወርወራቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ፈጥሮባቸዋል።
ለአርባ ዓመታት ከኖሩበት ሞቅ ያለ ቤታቸው በድንገት ተነስተው በኃላፊነት ጎደለው ሁኔታ ወደዚህ አካባቢ መወርወራቸው በእጅጉ እንዳሳዘናቸው የሚናገሩት እነዚህ ዜጎች የሚመለከተው አካልና ህዝቡ የእነሱን እውነተኛ እንግልት ያውቅ ዘንድ ጉዳዩ በዜና ሽፋን አግኝቶ አግባብ ያለው ማጣሪያ እንዲደረግላቸውና አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸው አጥብቀው ጠይቀዋል።
| መሠረት ሚድያ |



