ወጣቱ የት ገባ? ከታገተ ስድስት ወር የሞላው ወጣት ጉዳይ አነጋጋሪ መሆኑን ቀጥሏል
(መሠረት ሚድያ)- ባለፉት ጥቂት አመታት ሰዎች ታገቱ፣ ታፈኑ እና ታሰሩ የሚሉ መረጃዎች ለሀገራችን ህዝብ አዲስ እና አስደንጋጭ መሆናቸውን አቁመዋል።
በርካታ ግለሰቦች ጭምብል ባጠለቁ፣ የሲቪል ልብስ በለበሱ እንዲሁም በፀጥታ አካላት ተይዘው ተወስደው ሲሰወሩ በስፋት ይሰማል።
ባሳለፍነው ሳምንት እንኳን ሶስት ጋዜጠኞች ታፍነው ተወስደው ከቀናት በኋላ ከአዲስ አበባ ወጣ ባሉ ስፍራዎች ተለቀው መገኘታቸው ይታወሳል።
ዛሬ የምናቀርብላችሁ መረጃ ታፍኖ ከተወሰደ ስድስት ወር የሆነውን ወጣት ጉዳይ ነው።
ወጣቱ ሰይፈ ተ/ጊዮርጊስ የሚባል ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ነው። ቀይ ቦኔት የለበሱ አካላት የካቲት 6/2017 ዓ.ም ከምሽቱ 4 ስዓት አካባቢ መገናኛ 24 ኮንዶሚኒየም ውስጥ በመግባት አፍነው ወስደውታል።
የካቲት 9/2017 ዓ.ም እሁድ ቀን 6:00 ላይ ሁለት ሲቪል የለበሱና ባለ ቀይ ቦኔት ሰዎች አያት 49 ኮንዶሚኒየም ቤተሰቦቹ ቤት በመሄድ ፍተሻ እንዳረጉም ታውቋል።
"መርምረን እንለቀዋለን፣ ከኛ ጋር ነው ሰይፈ ያለው ብለው ወተው ሄዱ። ከዛ ወዲህ ግን የት እንደደረሰ አልታወቀም" በማለት ቤተሰቦቹ ይናገራሉ።
"ከዛ ስዓት ጀምሮ አዛውንት እናቱና መላው ቤተሰቦቹ እስር ቤቱን ሁሉ ቢያካልሉም የት እንደታሰረ ማወቅ አልተቻለም። ሁሉም ሰባዊነት የሚሰማው ለወንድማችን ድምፅ በመሆንና ለዓለም ዓቀፍ የሰባዊ መብት ተቋማት በማሳወቅ ተባበሩን" በማለት ተናግረዋል።
ወጣት ሰይፈ የቀድሞ የኢዜማ አመራሯ ገረት አራጌ እና ሌሎች ወጣቶች በተመሳሳይ ስዓት ታፍነው ሲወሰዱ አብሮ የታፈነ እና እስካሁን አድራሻው ያልታወቀ ወጣት ነው።
-መሠረት ሚድያ-




