በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ የተከሰተው ምንድነው?
(መሠረት ሚድያ)- በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን ስር የሚገኘው የዳንጉር ወረዳ ተከታታይ እና አሳዛኝ የሆኑ የንፁሀን ግድያዎችን የሚያስተናግድ ስፍራ ሆኖ ቀጥሏል።
ድርጊቱ በቅርብ አመታት ከመደጋገሙ የተነሳ ሚድያዎች እንኳን ሽፋን መስጠት እንዳቆሙ መረጃዎች ያሳያሉ።
መሠረት ሚድያ ከስፍራው የደረሰው አዲስ መረጃ እንደሚጠቁመው ባሳለፍነው አርብ ከ27 በላይ ንፁሀን ሰዎች በጉሙዝ ታጣቂዎች ከቤታቸው እና ከማሳ ላይ ተወስደው ተገድለዋል።
ያሰባሰብናቸው መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ገዳዮቹ ታጣቂዎች ሟቾቹን ከመኖርያ ቦታቸው አርቀው ጫካ ውስጥ ገድለዋል፣ የ20 ሰዎች አስከሬን ተገኝቶ መቀበሩ ታውቋል።
"ሁለት ሴቶች እስካሁን አልተገኙም፣ እስካሁን ከተገኙት ሟቾች ስድስቱ ሴቶች እንዲሁም አስራ አራቱ ወንዶች ናቸው። የአንድ ህፃን ልጅ ሬሳ የታየ እና የተመታበት ቦታ ቢታወቅም እስካሁን ግን አልተነሳም። ቤተሰብም ጫካ ቀረ በሚል ከሞቱ በላይ እየተጨነቁ ነው" በማለት አንድ የመረጃ ምንጭ ለሚድያችን ተናግረዋል።
የጉሙዝ ታጣቂ ናቸው የተባሉት አካላት አሰቃቂ በሆነ መልኩ ግድያውን መፈፀማቸው የተሰማ ሲሆን 'በሴቶች ላይ አሰቃቂ ነገሮችን ፈፅመዋል' ሲሉ ገልፀዋል።
"ታፍነው በሚሄዱበት ጊዜ የተወሰኑ ሰዎች አምልጠዋል። ከተገደሉት ውስጥ የቤተሰብ ኃላፊዎች የነበሩ ሲሆን አብዛኞቹ ከጎጃም እና ከጎንደር ወደ አካባቢው ለኑሮ የሄዱ ናቸው" በማለት ሌላ ምንጭ ጠቁመዋል።
ይህ ታጣቂ ቡድን ከአንድ ወር በፊት 13 ሰዎችን እንደገደለ የታወቀ ሲሆን በተለይ ክረምት ላይ የብዙ ሰዎችን ህይወት እንዳጠፋ በአካባቢው ነዋሪዎች ይነገራል።
"ገዳዩ በአካባቢው አመራር ሽፍን የሚደረግለት ቡድን ነው። በዚህ ወረዳ አንዳንድ የጉምዝ ማህበረሰብ አባላት 'ቀይ ሰው' በሚሉት ላይ የሚያደርሱት በደል እየከፋ መጥቷል" የሚሉት ነዋሪዎቹ ናቸው።
"መኪና ሲያልፍ ውሻ ከጮኸች ውሻዬ ደንግጣለች በሚል ካሳ የሚቀበሉ ሆነዋል፣ ለአንድ ኩንታል እህል መጫኛ ከገበሬው 450 ብር አስገድደው የሚቀበሉ ናቸው፣ አርሶ አደሩ በራሱ ጭኖ እያለ ሳይጭኑ 400 ብር በኩንታል ይቀበላሉ፣ መኪና ሲያልፋ ልትጭን ትችላለህ በሚል መንገድ አስቁመው ብር የሚቀበሉ ናቸው" ብለዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን 20 ገደማ ሰዎች የተገደሉባቸው ተከታታይ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ተከትሎ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የቅባት እህሎችን የሚያመርቱ የግል ባለሀብቶች እርሻዎቻቸውን ጥለው መውጣታቸው ከሳምንታት በፊት ተሰምቶ ነበር።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በአንጻራዊነት ሰላም ሰፍኖበት የነበረው መተከል ዞን፤ ካለፈው ግንቦት ጀምሮ ተከታታይ ጥቃቶች የተፈጸሙባቸው ዳንጉር እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚገኝበት ጉባ ወረዳዎች ናቸው።
ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በጥቃት እና ግጭቶች ሲታመስ የነበረው መተከል ዞን፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ትጥቅ ትግል ላይ ከነበሩት የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ እና የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ ጋር የፈጸማቸውን የሰላም ስምምነቶችን ተከትሎ መረጋጋት አሳይቶ ቆይቷል።
በዚህ ግድያ ዙርያ እስካሁን የክልሉም ሆነ የዞኑ ተቋማት ያሉት ነገር የለም። በዚህ ዙርያ የክልሉን የኮሚኒኬሽን ቢሮ ለማነጋገር ያረግነው ሙከራ አልተሳካም።
-መሠረት ሚድያ-




ምርት ሲደርስ ሁሌም ይህንን ያደርጋሉ !
አምራቾች ሲሸሹ ምርቱን ይጠቀማሉ !