(መሠረት ሚድያ)- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ በአዳዲስ ሆስፒታሎች የሠራተኞች ቅጥርን በተመለከተ በመሠረት ሚድያ ከአምስት ቀን በፊት የወጣውን የሙስና፣ የአድልዎ እና የሐሰተኛ ሰነድ አጠቃቀም ውንጀላዎችን 'መሠረተ-ቢስ እና ሐሰተኛ' ሲል አስተብሏል።
ቀደም ሲል ሚድያችን ያወጣው ዘገባ እንደሚያመለክተው በከተማ አስተዳደሩ አዳዲስ ሆስፒታሎች የቅጥር ሂደት ላይ ግልጽነት የጎደለው አሰራር መስፈኑን እና የፈጠራ ስሞችን በመጠቀም ሽፋን በመስጠት ህገ-ወጥ ቅጥሮች መፈጸማቸውን የህክምና ባለሙያዎችን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር።
ሆኖም የከተማ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ በሰጠው ማስተባበያ ውንጀላዎቹ የቅጥር ሂደቱን ለማደናቀፍ ያለሙ 'አሉባልታዎች' መሆናቸውን ገልጿል። በአሁኑ ወቅት በአዳዲሶቹ ሆስፒታሎች ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት ባለሙያዎች ከነባር ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች በውሰት የተመደቡ እንጂ እስካሁን ድረስ በቅጥር የተመደበ አዲስ ሠራተኛ አለመኖሩን ቢሮው አንስቷል።
ቢሮው የቅጥር ሂደቱ ግልጽነት ባለው እና ከሰው ንክኪ ነፃ በሆነ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ቢናገርም በጤናው ዘርፍ የሚደረጉ የቅጥር ሂደቶች ግልፅነት የጎደላቸውና በህገወጥ አሰራር የተሞሉ መሆናቸውን የጤና ባለሙያዎች እና አመልካቾች ለሚድያችን ተናግረዋል።
የጤናው ዘርፍ የሰውን ህይወት ከመታደግ አኳያ ከፍተኛ ጥንቃቄ እና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ምዘናን የሚጠይቅ ቢሆንም አሁን እየወጡ ያሉ መረጃዎች ግን ከዚህ ተቃራኒ የሆነ አሰራር በቢሮው ውስጥ እንደሰፈነ ይጠቁማሉ።
የከተማዋ አስተዳደር በቅርቡ አዳዲስ ሆስፒታሎችን ገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን እነዚህን ተቋማት በብቁ የሰው ሀይል ከማሟላት ይልቅ በሙስና የተዘፈቀ አሰራር መታየቱ ብዙዎችን እያሳሰበ ይገኛል።
በእነዚህ መረጃዎች መሰረት ለቅጥር የመጀመሪያው እና ዋነኛው መስፈርት የብሔር ተኮር አድልዎ መሆኑ ተገልጿል። በተለይም ከተወሰነ ብሔር መሆን እንደ ቅድመ ሁኔታ እየታየ ሲሆን በዚህ መስፈርት ውስጥ ለማይካተቱ አመልካቾች ደግሞ በተረፉት ክፍት ቦታዎች ላይ እስከ 50 ሺህ ብር የሚደርስ ጉቦ ማቅረብ ግዴታ እንደሆነ ተጋልጧል።
"ከዚህም ባሻገር ምንም አይነት ውድድር ሳይደረግ ከከፍተኛ ባለስልጣናት በሚመጣ "ሬኮመንዴሽን" (የድጋፍ ደብዳቤ) ብቻ ቀጥታ ወደ ስራ የሚገቡ ግለሰቦች መኖራቸው የችግሩን ጥልቀት ያሳያል" ብለው ቃላቸውን ለመሠረት ሚድያ የሰጡት አንድ በሂደቱ ያለፉ ግለሰብ ናቸው።
አክለውም "ይህ አይነቱ አድልዎ ሀገሪቱ ያፈራቻቸውን የህክምና ባለሙያዎች ተስፋ የሚያስቆርጥ እና ስር የሰደደ የመልካም አስተዳደር እጦትን የሚያሳይ ነው" ብለዋል።
ይህ ህገወጥ አሰራር በተለያዩ የከተማዋ የመንግስት ሆስፒታሎች ላይ በግልፅ ታይቷል ተብሏል። ለምሳሌ ያህል ለላፍቶ፣ ለኮልፌ እና ለአቤት ሆስፒታሎች የአንስቴዥያ ባለሙያዎችን ለመቅጠር ማስታወቂያ ወጥቶ አመልካቾች ምዝገባ ቢያካሂዱም ምንም አይነት የውድድር ፈተና ሳይሰጥ ቅጥሩ በድብቅ መፈጸሙን አረጋግጠናል።
በተመሳሳይ ሁኔታ ከ15 በላይ የሚሆኑ የድንገተኛ ቀዶ ጥገና ባለሙያዎች (IESO) የተፈተኑትን እና ብቁ የሆኑትን ወደ ጎን በመተው ምንም ሳይጠሩና ውድድር ውስጥ ሳይገቡ በቀጥታ መቀጠራቸው ተጋልጧል።
አንዳንዶች ደግሞ በፈተና ዝቅተኛ ውጤት አምጥተው ነገር ግን በገንዘብ ጉቦ አማካኝነት ስራውን ማግኘታቸው የጤና ቢሮውን አሰራር ጥያቄ ምልክት ውስጥ ከተቶታል። በተለይም እንደ አንስቴዥያ እና የድንገተኛ ቀዶ ጥገና የመሳሰሉ ከፍተኛ ትኩረት እና የህይወት አድን ክህሎት በሚጠይቁ የህክምና ዘርፎች ላይ ብቃት የሌላቸውን ሰዎች በሙስና መቅጠር ታካሚዎችን ለሞት አደጋ አሳልፎ ከመስጠት ተለይቶ አይታይም።
ከሁሉም በላይ አስገራሚው እና አሳዛኙ ድርጊት የተፈጸመው በ NICU/PICU (የጨቅላ ህጻናት እና የህጻናት ጽኑ ህክምና ክፍል) የቅጥር ሂደት ላይ መሆኑን መረጃው ያጋልጣል።
"የጽሁፍ ፈተና ሳይወስዱ ለቃል ፈተና ተመርጠዋል ተብሎ በጤና ቢሮው የተወጣው የስም ዝርዝር በአብዛኛው በእውነተኛው አለም የሌሉ፣ በሀሰት የተፈጠሩ የሰዎች ስሞች መሆናቸው ተረጋግጧል" የሚሉት ሌላኛው የመረጃ ምንጭ ናቸው።
ጤና ቢሮው ይህን ማስተባበያ ቢያወጣም በሶስት ክፍለ ከተሞች የሚገኙ 'የሚድያ ሰራዊት' የተቋሙን የፌስቡክ ገፅ በመውረር ተመሳሳይ መልዕክት በመፃፍ ላይ እንደሚገኙ ተመልክተናል።
"ይህንንም አሰራር ፍትሃዊ እና አካታች ለማስመሰል በማሰብ የተለያዩ የብሔር እና የእምነት ስብጥሮችን የሚያሳዩ እንደ ምኒልክ ሀብታሙ ተሰማ፣ መስፍን ታደሰ በለጠ፣ አዲሱ አበበ ብርሃኔ እና አብዱረዚቅ ሙጂብ የመሳሰሉ የፈጠራ ስሞችን ተጠቅመዋል" በማለት አክለዋል።
አክለውም "እውነታው ግን እነዚህ ስሞች ሽፋን ብቻ ሲሆኑ በእነሱ ቦታ ሆን ተብሎ የተፈለጉ ሰዎችን በጓዳ ለማስገባት የታለመ ሴራ መሆኑ ተጋልጧል" ብለዋል።
ጨቅላ ህጻናት በጽኑ በሚታከሙበት ክፍል ውስጥ እንዲህ ያለ ማጭበርበር መፈጸሙ በህፃናት ህይወት ላይ የሚደረግ አደገኛ ቁማር መሆኑን ባለሙያዎች በቁጭት ይገልጻሉ።
| መሠረት ሚድያ |



