"ወይ የኤሌክትሪክ መኪና ትገዛለህ፣ አለዛ ቆርቆሮ ባጃጅህን ታቅፈ ትቀመጣለህ"- የሐረር ባጃጅ አሽከርካሪዎች የገጠማቸው ፈተና
(መሠረት ሚድያ)- ከቅርብ ግዜ ወዲህ በሐረር ከተማ ነዋሪዎች ላይ በአስገዳጅነት እየተተገበሩ የሚገኙ ክስተቶች ቁጥራቸው እየጨመረ፣ ህዝቡም እየተማረረ እንደሆነ ይሰማል።
ዛሬ ሚድያችን የሚዳስሰው ሁለት ጉዳዮችን ነው: በአስገዳጅነት ከባጃጅ ወደ ኤሌክትሪክ ታክሲ የሚደረገው ጉዞ እንዲሁም ህንፃዎችን ከግንብ ወደ መስታወት የመቀየር ሂደት።
በሐረር ከተማ ውስጥ በርከት ያሉ የባጃጅ ተሽከርካሪዎች ይገኛሉ። ከሰባት ወር በፊት የባጃጅ ሹፌሮች አንድ አስገዳጅ ስብሰባ ተጠርተው ነበር።
በስብሰባው ላይ በከተማው ሀላፊዎች የተነሳው ጉዳይ በዋናነት 'የባጃጅ ተሽከርካሪዎችን ከተማ ውስጥ ማየት አንፈልግም፣ የኤሌክትሪክ መኪና እንድትገዙ ሁኔታዎችን እናመቻቻለን፣ ቆጥባቹ እና ተበድራችሁ ግዙ' የሚል እንደነበር እነዚህ አሽከርካሪዎች ለመሠረት ሚድያ ያስረዳሉ።
ይህን ያላረገ ግን ከሶስት አመት በኋላ ከተማ ውስጥ ገብቶ መስራት እንደማይችል ተነግሯቸዋል።
"ሐረርን የሚያክል ገጠርም የሌላት ከተማ... ሲቀጥል ከባጃጅና ከተወሰኑ የድሮ ፔጆ ተሽከርካሪዎች ውጪ የታክሲ ከገልግሎት የሚሰጥ የለም። በሰዐቱ እንደ ምክንያት የተቀመጠው የነዳጅ እጥረት ጉዳይ ነበር" በማለት አንድ አሽከርካሪ አስረድተዋል።
ሌላ አሽከርካሪ ደግሞ "እስከሚገባኝ ድረስ በታሰበው ልክ የሚቆጥብ ሰው አልተገኘም። አንድ ያለው Swift የተባለ ከድሬዳዋ የመጣ ድርጅት ነው፣ ዝቅተኛ የግዢ መኪና ያለው 2.5 ሚልየን ብር ነው። ምናልባት ለራይድ አገልግሎት ይሆን እንጂ ዝቅተኛውን ማህበረሰብ ለማገልገል የሚሆኑ መኪኖች አይደሉም" በማለት ተናግረዋል።
ግለሰቡ አክለውም "አሁን ከሰባት ወር በኋላ መጡና ደግሞ እነዚህን መኪኖች ለመግዛት የቁጠባ ቡክ ያልከፈተ እና ቡኩን ይዞ ማይንቀሳቀስ የባጃጅ ሹፌር እንቀጣለን ማለት ጀመሩ። ቁጠባው ቡክ ስትከፍት የምዝገባ 1,000 ብር እና 10 አክስዮን ማለትም 10 ሺህ ብር መክፈል ይጠበቅብሀል። የወር ዝቅተኛ ቁጠባ 1,000 ይጠበቅብሀል" ብለው ሁኔታውን ተናግረዋል።
እነዚህ የባጃጅ አሽከርካሪዎች እንደሚሉት 60 ሚሊዮን ብር በሚሸጥ ሊንከን ናቪጌተር በተባለ ቅንጡ መኪና የሚንቀሳቀሱት የሐረሪ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ኦርዲን በድሪ ጉዳዩን በቀጥታ ይከታተሉታል።
"ስብሰባ ላይ ወይ የኤሌክትሪክ መኪና ትገዛለህ፣ አለዛ ቆርቆሮ ባጃጅህን ታቅፈ ትቀመጣለህ ነው የሚሉህ። ድምፅ ሁኑን" ብለዋል።
ሌላኛው ጉዳይ ደግሞ በሐረር ከተማ ውስጥ የሚገኙ ህንፃዎች ፊታቸው ፈርሶ ሙሉ በሙሉ በመስታወት እንዲሰራ የሚያዘው አዲስ ህግ ነው።
በዚህ አዲስ አሰራር ምክንያት በርካታ ህንፃዎች ፈርሰው እየተሰሩ መሆኑ እና ወጪውም በህንፃው ባለቤቶች መሆኑ ለከፍተኛ ወጪ እንደዳረጋቸው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
ፎቶ: ፋይል
መረጃን ከመሠረት!



