በፖለቲካ ተሳትፎው ምክንያት ከስምንት ጊዜ በላይ ታስሮ የነበረው ወጣት ናትናኤል ያለምዘውድ ሀገር ጥሎ ለመውጣት መገደዱን ተናገረ
(መሠረት ሚድያ)- በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት በሚደረጉ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችና የተቃውሞ መድረኮች ላይ በግንባር ቀደምትነት ሲሳተፉ ከነበሩት ወጣት ፖለቲከኞች መካከል ናትናኤል ያለምዘውድ አንዱ እንደሆነ ይነገራል።
ይህ ወጣት ፖለቲከኛ በተለይም በሰማያዊ ፓርቲ እንዲሁም በኋላ ደግሞ በባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ውስጥ በነበሩት የድርጅት መዋቅሮች ውስጥ በአመራርነት ደረጃ በመደደብ ንቁ ተሳትፎ ሲያደርግ እንደነበር ይታወቃል።
ሆኖም ግን ያንፀባርቀው የነበረው የፖለቲካ አመለካከትና የሚያደርገው ተሳትፎ ከፀጥታ አካላትና ከባለሥልጣናት ጋር ላለመግባባት ዳርጎት እንደነበር ተገልጿል።
በዚህም ምክንያት በየጊዜው ይደርስበት በነበረው ጫና ሳቢያ ከስምንት ጊዜ በላይ መታሰሩንና ለተለያዩ አካላዊ እንዲሁም ሥነ-ልቦናዊ እንግልቶች መዳረጉን ያሰባሰብናቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ናትናኤል ያለምዘውድ በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉበት እስራቶች ወቅት በአዋሽ አርባ በሚገኘው የማሰቃያ ስፍራ ጭምር ለረጅም ወራት ታስሮ እንደቆየና እዚያም በነበረበት ጊዜ ከባድ ድብደባና እንግልት ይፈጸምበት እንደነበር ገልጿል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የደህንነት ሁኔታ እየከፋ በመምጣቱ ምክንያት በፀጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ክትትል ሲደረግበት እንደነበርና የመግደል ሙከራም ጭምር እንደተደረገበት ለሚድያችን አመልክቷል።
በተለይም ታርጋ የሌላቸው የተለያዩ መኪኖችን የሚጠቀሙ የፀጥታ አባላት በመኖሪያ ቤቱ አካባቢ ደጋግመው በመመላለስ ከባድ ዛቻዎችን ይፈጽሙበት እንደነበርና ይህም ለሕይወቱ አደጋ መደቀኑን ገልጿል።
"በአገሪቱ ውስጥ የሕግ የበላይነትና የዜጎች ደህንነት ዋስትና ማጣት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ምክንያት በነፃነት የመንቀሳቀስና የመኖር መብቴ በመገፈፉ ከሀገር ተሰድጃለሁ" በማለት ተናግሯል።
በሀገር ውስጥ ህግን መሠረት ያደረገ አሰራርና የአሰራር ሥርዓት እንጥፍጣፊው እንኳ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ መቆየት ሕይወቱን አደጋ ላይ እንደሚጥለው በመገንዘብ የፀጥታ አካላቱ ከባድ እርምጃ ሳይወስዱበት አስቀድሞ ሀገሩን ጥሎ ለመውጣት መወሰኑን ጨምሮ ተናግሯል።
ይህ በወጣቱ ፖለቲከኛ ላይ የደረሰው እንግልትና ስደት በኢትዮጵያ ውስጥ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና ግለሰቦች ላይ የሚደርሰውን የመብት ገፈፋና የደህንነት ስጋት አመላካች እንደሆነ ይነገራል።
በርካታ ወጣቶችና የፖለቲካ ተሳታፊዎች በራሳቸው ሀገር በነፃነት ሀሳባቸውን የመግለጽና የመደራጀት መብታቸው በመጠበቁ ምክንያት ተመሳሳይ የኃይል እርምጃዎችና እስራቶች ሰለባ ሲሆኑ ይስተዋላል።
| መሠረት ሚድያ |


