በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ውስጥ ወደቀ ስለተባለ የጦር ጄት ሲሰራጩ የቆዩት መረጃዎች ትክክለኛ መሆናቸውን ኢትዮጵያ ቼክ አረጋገጠ
(መሠረት ሚድያ)- በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ውስጥ ወደቀው ስለተባለ የጦር ጄት በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሲሰራጩ የቆዩት መረጃዎችን አስመልክቶ ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ዝርዝር ማጣራት የጄቱ ምስሎችና ቪዲዮዎች እውነተኛ መሆናቸውን አረጋግጧል።
ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በቦራ ወረዳ የወደቀውን የጦር ጄት ስብርባሪ አካል ብቻውን እንዲሁም የታጠቁ ሰዎች በስብርባሪው ላይ ቆመው የሚያሳዩ በርካታ ምስሎች እና ቪዲዮዎች በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በስፋት ሲጋሩ ቆይተዋል።
የመረጃው መሰራጨትን ተከተሎ አንዳንዶች የጦር ጄቱ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ታጣቂዎች ተመቶ መውደቁን በመጥቀስ ምስሎቹን ያጋሩ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ ምስሎቹ እና ቪዲዮዎቹ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም ኤአይ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተሰርተው የቀረቡ ናቸው ሲሉ ተከራክረዋል።
በተጨማሪም ከ500 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ደመቀ ነጋሳ ኩቤ የተሰኘው የፌስቡክ ገጽን ጨምሮ ሌሎች አካላት ምስሉ የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ጄት እንደማያሳይ እና የሚሰራጨው ዜና በፍጹም ውሸት መሆኑን በመግለጽ መረጃውን አስተባብለውት ነበር።
ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ቼክ በምስሎቹ እና በቪዲዮዎቹ ላይ ባደረገው ጥልቅ ማጣራት የቀረቡት ምስሎችም ሆኑ ቪዲዮዎች በሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም በቅንብር የተሰሩ እንዳልሆኑ እና ከዚህ ቀደም በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ተጋርተው የማያውቁ አዳዲስ መረጃዎች መሆናቸውን አረጋግጧል።
በመረጃ ማጣራቱ ሂደት መሰረት የወደቀው የጦር ጄት ኤሮ ኤል-39 አልባትሮስ በመባል የሚታወቅ የቼክ ሪፐብሊክ ስሪት ሲሆን ይህ ጄት በስፋት ለስልጠና አገልግሎት የሚውል እና ለአየር ላይ ውጊያ፣ ለመሬት ላይ ኢላማዎች ጥቃት እንዲሁም ለስለላ አገልግሎት ሊውል የሚችል የጦር መሳሪያ ነው ተብሏል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ይህንን የጄት አይነት ለስልጠና አገልግሎት እንደሚጠቀም ቀደም ሲል የገለጸ ሲሆን ጄቱ የዛሬ ስድስት ወር ገደማ በተከበረው የአየር ኃይሉ የ90ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ትርዒት ካሳዩት በርካታ ጄቶች መካከል አንዱ እንደነበር ተመልክቷል።
ኢትዮጵያ ቼክ የተከሰከሰውን የጄት ስብርባሪ በአየር ኃይሉ ክብረ በዓል ላይ ትርዒት ካሳዩት ሌሎች አልባትሮስ ጄቶች ጋር በማነጻጸር ባደረገው የንፅፅር ፍተሻ ሁለቱም ተመሳሳይ የቀለም ስብጥር እንዳላቸው ማረጋገጥ ችሏል።
በተደረገው ፍተሻም በጄቶቹ ስር የሚገኘው ሰማያዊ ቀለም፣ በክንፎቹ ጫፍ ላይ ያሉት ቀይ እና ቢጫ ቀለማት እንዲሁም በጅራታቸው ጫፍ ላይ የሚገኘው ቢጫ ቀለም ቅብ ሙሉ በሙሉ ተመሳሳይ መሆናቸው ተረጋግጧል።
እነዚህ የተጠቀሱት የቀለም ምልክቶች እና በጄቱ ስብርባሪ ምስል ላይ የሚታየው የመሬት አቀማመጥ መመሳሰል፣ የወደቀው ጄት ከምንም በላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ንብረት መሆኑን የሚያመላክቱ አሳማኝ ማስረጃዎች ናቸው ብሏል።
ሆኖም ግን የጦር ጄቱ በታጣቂዎች ተመቶ መውደቁን ወይም በቴክኒክ ችግር ምክንያት የተከሰከሰ መሆኑን በተመለከተ እስካሁን ድረስ በማስረጃ የተደገፈ ግልጽ ምላሽ ያላገኘ ሲሆን በጉዳዩ ላይ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት የሰጡት ይፋዊ መግለጫ የለም።
ምንጭ፦ ኢትዮጵያ ቼክ (Ethiopia Check)



