ወደ መቀሌ እና አክሱም ከተሞች የሚደረጉ የአየር በረራዎች በዛሬው ዕለት ተቋርጠው የዋሉ ሲሆን የነገ በረራዎችም እንደተሰረዙ ሚድያችን ማምሻውን አረጋግጧል
(መሠረት ሚድያ)- ወደ ትግራይ የሚደረጉ የአየር በረራዎች ከዛሬ ጀምሮ እንደሚቋረጡ ሚድያችን በትናንትናው ዕለት ማስነበቡ ይታወሳል።
"ከበላይ አካል በመጣ ትዕዛዝ ነው" በተባለለት በዚህ የበረራ ስረዛ በርካቶች ከጉዞ እንደተስተጓጎሉ የታወቀ ሲሆን አንዳንድ ነዋሪዎች እና የአለም አቀፍ ድርጅቶች ሰራተኞች ከክልሉ ለመውጣት ጥድፊያ ላይ እንዳሉ ሚድያችን ሰምቷል።
አሁን ማምሻውን የደረሰን መረጃ እንደሚጠቁመው ደግሞ ወደ መቀሌ እና አክሱም ከተሞች የሚደረጉ የአየር በረራዎች በዛሬው ዕለት ሙሉ በሙሉ ተቋርጠው የዋሉ ሲሆን የነገ በረራዎች ይካሄዳሉ ተብሎ ተስፋ ቢደረግም እነሱም እንደተሰረዙ ሚድያችን አረጋግጧል።
ነገ እና ከነገ ወዲያ ለሚደረጉ በረራዎች እስከ ቅርብ ሰአታት ድረስ ትኬት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ድረ-ገፅ ሲሸጥ እንደነበር ተመልክተናል።
የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤ ኤፍ ፒ (AFP) ወደ ትግራይ የሚደረጉ በረራዎች የተሰረዙት አዲስ በተቀሰቀሰ ግጭት መሆኑን መስማቱን ዛሬ ዘግቧል።
የአየር መንገድ ምንጮቻችን የመቀሌ እና አክሱም የነገ በረራዎች እንደማይኖሩ አረጋግጠው ወደ ሁመራ የሚደረግ በረራ ግን እንደሚኖር ጠቁመዋል፣ ይህም ግን በመጪው ጥቂት ሰዓታት ውስጥ ሊቀየር እንደሚችል ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአንድ መንገደኛ የበረራ መሰረዝን በተመለከተ የላከውን ኢሜይል የተመለከትን ሲሆን በረራው ላልተወሰነ ግዜ መሰረዙን ይገልፃል።
ሚድያችን ከአየር እንዳረጋገጠው የመጨረሻው የትግራይ ቋሚ በረራ ትናንት ምሽት 3:30 ላይ ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ የተደረገ ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ ግን ሁሉም በረራዎች እንደተሰረዙ ታውቋል።
ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ ክልል ከተሞች የሚደረጉ የሀገር ውስጥ በረራዎች እንደቀጠሉ የታወቀ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስልክ ጥሪ ማዕከል የሆነው 6787 ሁሉም የትግራይ በረራዎች እንደታገዱ እንደሚያረጋግጥ ታውቋል።
ከዛሬ ምሽቱ የሽሬ የመጨረሻ በረራ ቀደም ብሎ የበረራ ቁጥሩ 'ET299' የሆነ የመቀሌ- አዲስ አበባ መደበኛ (scheduled) በረራ እንደነበር ምንጮቻችን አስረድተው በተጨማሪም አንድ መደበኛ ያልሆነ (unscheduled) በረራ ከመቀሌ ተደርጎ እንደነበር አረጋግጠዋል።
የአየር በረራ እገዳው ከምን ጋር የተያያዘ እንደሆነ እስካሁን በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ በፌደራል መንግስት እንዲሁም በአየር መንገዱ ይፋ ያልተደረገ ቢሆንም በመንግስት እና በክልሉ ባሉ ሀይሎች መካከል ያለው ውጥረት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል መረጃዎች ያሳያሉ።
-መሠረት ሚድያ-




