ከቴህራን እስከ ባብ ኤል ማንደብ፡ የኢራን ጦርነት በአፍሪካ ቀንድ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ
አቅራቢ፡ ሱራፌል ጌታሁን የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር፣ ተመራማሪ እና የፖለቲካ ተንታኝ
አጠቃላይ እይታ
እ.ኤ.አ. በመጋቢት 2026 የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ካሜኔይ በአሜሪካ እና በእስራኤል በተፈጸመ የአየር ጥቃት መገደላቸው የመካከለኛው ምስራቅን የጂኦፖለቲካል ሚዛን ሙሉ በሙሉ ለውጦታል። ይህ ክስተት ከአንድ ሀገር መሪ ሞት በላይ የሆነ ትርጉም ይዟል። ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ የኢራን የውጭ ፖሊሲን በቀጥታ የመሩት ካሜኔይ የተፈጥሮ ሞት እንኳ ቢሆን ኖሮ በስርአቱ ላይ ከፍተኛ እንቅጥቅጥ ሊፈጥር የሚችል ነበር። በዚህ ጊዜ ግን ጥቃቱ በቀጥታ በውጭ ኃይሎች የተፈጸመ በመሆኑ፣ ኢራን በድንበር አቋርጦ ወደሚደረግ ምላሽ ስትገባ፣ የመላው ከመካከለኛው ምስራቅ የቀጠናው የደህንነት ስርዓት ወደ አዲስ የግጭት መሃከል ገብቷል።
የዚህ ጽሁፍ ዋና ነጥብ ይህ ግጭት ከመካከለኛው ምስራቅ ድንበር አልፎ የአፍሪካ ቀንድን እንዴት እንደሚነካ መተንተን ነው። የአፍሪካ ቀንድ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጡ ከአረብ ባሕረ ገብ መሬት ጋር በቀይ ባህር በኩል ይዋሰናለ። ይህ ባህር ከአለም ንግድ 23 በመቶውን የሚሸፍን የስትራቴጂክ ኮሪደር ነው። ስለዚህ በመካከለኛው ምስራቅ የሚፈጠር ማንኛውም ወታደራዊ ግጭት ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆነ ተጽዕኖ በአካባቢ ሊያሳድር ይችላል።
በዚህ ትንታኔ ውስጥ አራት ዋና ዋና ነጥቦችን እንመረምራለን፡- (1) የኢራን ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆነ ተጽዕኖ በቀጠናው ውስጥ ያለው ውስንነት፣ (2) በቀይ ባህር የማጓጓዣ መስመር ላይ የሚደርሰው ስጋት እና የሂውቲ ቡድን ሚና፣ (3) የባህረ ሰላጤ ሀገራት ትኩረት ወደ ውስጥ መመለስ በሱዳን፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ጉዳዮች ላይ የሚፈጥረው ቀውስ፣ እንዲሁም (4) የአፍሪካ ህብረት እና የክልሉ ሀገራት ለዚህ ሁኔታ ያላቸው አቋም እና የወደፊት ትንበያ።
1. የኢራን ተጽዕኖ በአፍሪካ ቀንድ፡ ከገጽታ በላይ ያለው እውነታ
በአለም አቀፍ የፖለቲካ ንግግሮች ውስጥ ኢራን በአፍሪካ ቀንድ ጠንካራ ተጽዕኖ እንዳላት የሚገልጽ አባባል ተደጋግሞ ይሰማል። ነገር ግን ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያለውን ተጨባጭ የፖለቲካ እውነታ ስንመረምር፣ የኢራን ተጽዕኖ ከሚታሰበው በጣም ያነሰ እንደሆነ እናያለን። በተለይም በ2015 የኢራን የባህር ኃይል መርከብ “ሳቪዝ” በቀይ ባህር መታይት ሲጀምር፣ ይህ እርምጃ የክልሉ ሀገራት ከኢራን ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲገመግሙ አድርጓቸዋል።
በዚሁ ወቅት ሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ ሀገራትን በገንዘብ እና በዲፕሎማሲ(ATM Diplomacy )የማቀራረብ ስራ ከፍ አደረጉ። ይህን ተከትሎ ሱዳን በ2016 ከኢራን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ አቋረጠች። ጅቡቲ እንዲሁም በተመሳሳይ አመት ከኢራን ጋር የነበራትን ግንኙነት ወደ, ቻርጅ ዲፍዌር(Charge de affair) ወይም ጉዳያ አስፈጻሚ ደረጃ ዝቅ አደረገችው። ኤርትራ ከሳውዲ አረቢያ ጋር በጥምረት ስትሄድ፣ ኢትዮጵያም በአብይ አህመድ ዘመን ወደ ባህረ ሰላጤ ሀገራት በተለይ ከተባብርቱ አረብ ኤምሬትስ ጋር የነበራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማጠናክር ቀጥላልች ።
እነዚህ ክስተቶች የሚያሳዩት ከአስር አመታት በፊት የነበረው የኢራን ተጽዕኖ በቀጠናው ውስጥ ከፍተኛ ውድቀት እንደደረሰበት ነው። በአሁኑ ጊዜ የኢራን ፖሊሲ በአፍሪካ ቀንድ በሁለት ዋና ዋና ምሰሶዎች ላይ የተመሰረተ ነው። አንደኛው፡ በየመን የሚገኘውን የአንሳር አላህ (ሂውቲ)ታጣቂ ቡድን በጦር መሳሪያ እና በስለላ መደገፍ ነው። ሁለተኛው ደግሞ፡ በክልሉ ውስጥ ያሉ ከአረብ ሀገራት ጋር የማይጣጣሙ ኃይሎችን በተወሰነ ደረጃ ድጋፍ ማድርግ ወይም ማበረታታት ነው።
አሁን ላይ በሚስተዋለው ክስተት በተለይ ከካሜኔይ ሞት በኋላ ኢራን ወደ ቀጥናው የመግባት አቅም የላትም። ምክንያቱም ኢራን አሁን ከእስራኤል እና ከአሜሪካ ጋር በቀጥታ ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ስትገባ፣ ሁሉም ሃብቷ ወደ ጦር ግንባር ማዞር ሰልሚኖርባት ነው። በዚህ ሁኔታ ከኢራን ወደ አፍሪካ ቀንድ የሚፈሰው የገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ድጋፍ በእጅጉ ይቀንሳል። ስለዚህ የኢራን ጦርነት በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያለው ቀጥተኛ ተጽዕኖ ውስን እንደሆነ ልንገልጽ እንችላለን። ይልቁንም ኢራን በቀጠናው ተጽዕኖዋን ልታሳድር የየምትችለው በቀጥተኛ ባልሆኑ መንገዶች ሊሆን እንደሚችል ይገመታል ፡፡
2. የቀይ ባህር የማጓጓዣ መስመር፡ የግጭቱ እምብርት
የቀይ ባህር ስልታዊ(Strategic)አቀማመጥ ከግብፅ ሱዌዝ ቦይ ጀምሮ እስከ ባብ ኤል ማንደብ ድረስ የሚዘረጋ ሲሆን፣ ይህ መስመር ከአውሮፓ፣ ከእስያ እና ከአፍሪካ ገበያዎች ጋር የሚያገናኝ የንግድ ደም ቧንቧ ነው። በየቀኑ ከ6 እስከ 8 ሚሊዮን በርሜል ዘይት በዚህ መስመር ይጓጓዛል። በካሜኔይ ግድያ ምክንያት የተፈጠረው ጦርነት በቀጥታ ይህንን የንግድ መስመር ስጋት ውስጥ ጥሎታል ፡፡
እንድሚታወቀው ከዚህ ቀደም ክኖቬምበር 2023 ጀምሮ የሂውቲ ቡድን በእስራኤል ላይ ከተፈጸመበት ጥቃት ጋር በማገናኘት በቀይ ባህር የሚጓዙ መርከቦችን ማጥቃቱ ይታወቃል ። በወቅቱ ይህን ጥቃት በአሜሪካ የሚመራው የባህር ኃይል ጥምረት እንኳ ሙሉ በሙሉ ማስቆም አልቻለም ነበር። አሁን ደግሞ በኢራን ላይ የሚደረገው ጦርነት በሂውቲዎች ላይ ቀጥተኛ ጫና እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል። ወይም በተቃራኒው ኢራን በዚህ የተጠናከረ ግፊት ውስጥ እያለች ሂውቲዎችን ቀይ ባህርን ሙሉ በሙሉ ለማዘጋት ልትጠቀምባቸው ትችላለች የሚሉ ስጋቶች አሉ ።
ይህ ሁኔታ በአፍሪካ ቀንድ በኩል በርካታ አደጋዎችን ሊደቅን ይችላል ።
አንደኛ፡ የሶማሊያ አልሻባብ እንቅስቃሴ – እንድሚታወቀው ሂውቲዎች ከአልሻባብ ጋር ባለፉት ዓመታት የመሳሪያ ንግድ እና የስለላ ልውውጥ ሲያደርጉ ቆይተዋል። የኢራን ጦርነት እየተባባሰ ሲሄድ፣ ሂውቲዎች አልሻባብን በመጠቀም በሶማሊያ የባህር ዳርቻ የሚገኙ መርከቦችን ሊያጠቁ ወይም የባህር ወንበዴዎችን እንደገና ሊያነቃቁ ይችላሉ። በሌላ በኩል የሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግስት በአልሻባብ ላይ እያካሄደ ያለውን ዘመቻ ውስብስብ ያደርገዋል።
ሁለተኛ፡ የጅቡቲ ገለልተኝነት – ጅቡቲ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ በጣም ስልታዊ የሆነች ሀገር ናት። የአሜሪካ ትልቁ ወታደራዊ ሰፈር በአፍሪካ “Camp Lemonnier” የሚገኘው በጅቡቲ ነው። በተጨማሪም ቻይና፣ ፈረንሳጅ፣ ጣሊያን፣ ጃፓን እና ሳውዲ አረቢያ በጅቡቲ ወታደራዊ የጦር ሰፈር አላቸው። ጦርነቱ እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ የሂውቲዎች ሚሳኤል እነዚህን ሰፈሮች ኢላማ ቢያድረግ ፥ ጅቡቲ ከኢራን ጋር የሚጋጭ አቋም ከመውሰድ ይልቅ ገለልተኝነቷን ተጠብቃለች ተብሎ አይጠበቅም።ይህም በመሆኑ የጅቡቲ አቋም የቀጠናው ሀገራት በውጭ ኃይሎች ግፊት ጦርነት ውስጥ ለመግባት ፈቃደኝ አለምሆናችውን ቢያመላክትም ጫናው እያይለ ከመጣ ፍቃደኝ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ደግሞ ቀጠናው ለትልቅ የድህንነት ስጋት ሊዳርግው ይችላል ፡፡
3. የባህረ ሰላጤ ኃይሎች ትኩረት ወደ ውስጥ መመለስ እና በቀጠናው ግጭቶች ላይ ያለው ተጽዕኖ
ከካሜኔይ ሞት በኋላ የሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ዋነኛ ትኩረት ወደ ራሳቸው የደህንነት ጥበቃ ዞሯል። ይህ በአፍሪካ ቀንድ በርካታ መዘዞችን ሊያስከትል ይችላል።
ሀ. የሱዳን ጦርነት እና የውጭ ድጋፍ መቀነስ
ሱዳን ከኤፕሪል 2023 ዓ.ም ጀምሮ በሱዳን ጦር ኃይሎች (SAF) እና በፈጣን ድጋፍ ሃይሎች (RSF) መካከል በተካሄደ የእርስ በርስ ጦርነት ተውጣለች። ከጦርነቱ መጀመሪያ ጀምሮ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች RSFን በጦር መሳሪያ እና በገንዘብ ስትደግፍ ቆይታለች። ሳውዲ አረቢያ እንዲሁም ሁለቱንም ወገኖች በማስታረቅ የራሷን ተጽዕኖ ለማስጠበቅ ሞክራለች።
አሁን ከኢራን ጋር ያለው ግጭት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ፣ ሁለቱም የባህረ ሰላጤ ሀገራት በሱዳን ላይ የሚያደርጉትን ወታደራዊ እና ገንዘብ ድጋፍ ለመቀነስ ይገደዳሉ። ይህ ደግሞ በሱዳን እርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ሚዛኑን የሚጠብቅ ኃይል እንዳይኖር በማድረግ ጦርነቱ እንዲራዘም ወይም አንደኛው ወገን ሌላውን ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ጥረት ሊያፋጥን ይችላል።
በሱዳን ውስጥ የኢራን ቀጥተኛ ተሳትፎ ውስን ቢሆንም፣ ከሱዳን ጦር ጋር ባለፉት አመታት የስለላ ትብብር አድርጓል። በአሁኑ ወቅት የሱዳን ጦር ከኢራን ጋር ያለውን ግንኙነት መልሶ ለማቋቋም እየሞከረ ቢሆንም፣ በኢራን ላይ ከሚደረገው ጦርነት የተነሳ ይህ ጥረት ስኬታማ ላይሆን ይችላል።
ለ. ኢትዮጵያ-ኤርትራ ግንኙነት እና የቀይ ባህር መዳረሻ ጥያቄ
ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ የባህር ኃይል ለማቋቋም ከሶማሊላንድ ጋር በጥር 2024 ዓ.ም የተፈራረመችው ስምምነት ከዚህ ቀደም ከባህረ ሰላጤ ሀገራት ከፍተኛ ተቃውሞ አጋጥሞት ነበር። በተለይም ግብፅ እና ኤርትራ ስምምነቱን በመቃወም ከሶማሊያ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ላይ ግፊት አድርገዋል።
አሁን የባህረ ሰላጤ ሀገራት ትኩረታቸውን ወደ ኢራን ጦርነት ሲያደርጉ፣ ኢትዮጵያ ይህንን ክፍተት በመጠቀም የሶማሊላንድ ስምምነቷን ወደ ተግባር ለመቀየር እድል ልታገኝ ትችላልች። በተመሳሳይ ጊዜ ኤርትራ በዚህ ጦርነት ምክንያት የምታገኘው የውጭ ድጋፍ ሊቀንስ ይችላል። ስለዚህ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል በአሁኑ ወቅት ያለው ውጥረት ወደ ለይለት ግጭት ሊሸጋገር የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል። ይህ ደግሞ የአፍሪካን ቀንድ ወደ ሌላ የጦርነት ዑደት ሊገፋት ይችላሉ።
ሐ. የሶማሊላንድ እውቅና እና የእስራኤል ሚና
እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 2025 እስራኤል ሶማሊላንድን እንደ ሉዓላዊ ሀገር እውቅና ሰጠች። ይህ እርምጃ በአፍሪካ ህብረት እና በአረብ ሊግ ዘንድ ተቀባይነት ባያገኝም፣ እስራኤል ከኤሚሬትስ እና ከሳውዲ አረቢያ ጋር ባላት ግንኙነት ይህንን እውቅና ለማስፈን ትጥራለች።
በኢራን ጦርነት ምክንያት እስራኤል በክልሉ ያላት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሊጨምር ይችላል። የአሜሪካ ጦር ሰፈር ከጅቡቲ ወደ ሶማሊላንድ በርበራ ወደብ ሊዛወር እንደሚችል የሚገልጹ ዘገባዎች አሉ። ይህ ከሆነ ግን የሂውቲ ቡድን ሶማሊላንድን እንደ ኢላማ ሊያደርጋች ይችላል። ምክንያቱም የሂውቲ መሪ አብደል ማሊክ አል ሂውቲ ቀደም ሲል “በሶማሊላንድ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም የእስራኤል ወታደራዊ መገኘት ህጋዊ ኢላማ ይሆናል” በማለት አስጠንቅቋል።
4. የአፍሪካ ህብረት እና የክልል ሀገራት አቋም፡ የድምፅ ልዩነት
የኢራን ጦርነት በአፍሪካ ህብረት እና አፍሪካ ቀንድ ሀገራት መካከል የተለያየ አቋም እንዲኖር አድርጓል። በአንድ በኩል የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት (ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ) በኢራን ላይ ጠንከር ያለ ትችት ሰንዝረዋል። ነገር ግን ግጭቱን ስለጀመሩት አሜሪካ እና እስራኤል ምንም አልተናገሩም። ይህ አቋም ከባህረ ሰላጤ አገራት እና ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማስጠበቅ ነው።
በሌላ በኩል ደቡብ አፍሪካ እና ሴኔጋል የአሜሪካን እና እስራኤልን የቅድመ-አጥቂነት እርምጃ በመቃወም ዓለም አቀፍ ህግን አስመልክተው አቋም ወስደዋል። ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ “የቅድመ-መከላከያ ጥቃት በአለም አቀፍ ህግ አይፈቀድም” በማለት የአሜሪካን እርምጃ ተችተዋል። ይህ የአፍሪካ ህብረት በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያለውን የጋራ አቋም አለመኖር ያሳያል።
ምዕራብ አፍሪካ ሀገራት (ናይጄሪያ፣ ጋና) ጥንቃቄ የተሞላበት አቋም ወስደዋል። ሁለቱንም ወገኖች እንዲታቀቡ እና ዓለም አቀፍ ህግን እንዲከተሉ ጥሪ አድርገዋል። ነገር ግን ከኢራን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የላቸውም።
5. የኢኮኖሚ ተጽዕኖ፡ ከነዳጅ ዋጋ እስከ ገንዘብ ዝውውር
የኢራን ጦርነት በአፍሪካ ቀንድ ኢኮኖሚ ላይ በርካታ ተጽዕኖዎች እንደሚኖሩት ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።
የነዳጅ ዋጋ መጨመር - የሆርሙዝ ውስጥ የሚተላለፈው 20% የአለም ነዳጅ አቅርቦት ስለተስተጓጎለ፣ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ኢትዮጵያ እና ኬንያ ነዳጅ ከውጭ የሚገቡ ሀገራት በመሆናቸው የንግድ ትርፍ እጥረት እንደሚያጋጥማቸው ይጠበቃል።
የገንዘብ ምንዛሬ መዋዥቅ - በኢራን ጦርነት ምክንያት የአሜሪካ ዶላር ከፍ ይላል ተብሎ ስለሚጠበቅ፣ የአፍሪካ ምንዛሪዎች ተጽዕኖ ሊደርስባቸው ይችላል።
የንግድ መስመሮች መቋረጥ - ቀይ ባህር ከተዘጋ የኢትዮጵያ ንግድ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊደርስበት ይችላል። ኢትዮጵያ የውጭ ንግዷን 95 በመቶ የምታከናውነው በጅቡቲ ወደብ ነው። ይህ ወደብ በሂውቲዎች ጥቃት ከተዘጋ ኢትዮጵያ ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ ሊግጥማታ ይችላል ።
የገንዘብ ዝውውር መቀነስ - በባህረ ሰላጤ የሚኖሩ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ዜጎች በየወሩ ወደ አገራቸው የሚልኩት ገንዘብ የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚን ለማነቃቃት ትልቅ ሚና ይጫወታል። በባህረ ሰላጤ ሀገራት ውስጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በጦርነቱ ምክንያት ቢቀንስ፣ ወደ አፍሪካ ቀንድ የሚላከው ገንዘብ ይቀንሳል::
6. ወደፊት ሊኖሩ የሚችሉ ስጋቶች ፡ ሶስት የወደፊት ትንበያዎች
የኢራን ጦርነት አፍሪካ ቀንድን በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ እንዴት እንደሚቀርጸው ሶስት ዋና ዋና ሁኔታዎችን መገመት እንችላለን።
ሁኔታ አንድ፡ የተወሰነ ጦርነት እና የክልል መረጋጋት መቀጠል
ኢራን እና እስራኤል/አሜሪካ ጦርነቱን በአየር እና በሚሳኤል ጥቃት ብቻ ከገደቡት፣ እና የምድር ላይ ወረራ ካልፈጸሙ፣ አፍሪካ ቀንድ ከባድ ቀውስ ሊያጋጥመው ይችላል። በዚህ ሁኔታ የሂውቲዎች እንቅስቃሴ በቀይ ባህር ቢቀጥልም፣ ከባህረ ሰላጤ ሀገራት ድጋፍ በመቀነሱ ምክንያት የሱዳን ጦርነት እንደሚራዘም እና በኢትዮጵያ-ኤርትራ ድንበር ላይ ያለው ውጥረት እንደሚቀጥል ይጠበቃል። ነገር ግን ግልጽ ጦርነት አይነሳም።
ሁኔታ ሁለት፡ የጦርነት መስፋፋት እና የቀይ ባህር መዘጋት
ኢራን በቀጥታ የሂውቲዎችን የሚሳኤል አቅም ካሳደገች፣ እና ሂውቲዎች በጅቡቲ ወደብ እና በሶማሊላንድ የባህር ዳርቻ ላይ ጥቃት ከፈጸሙ፣ የቀይ ባህር የማጓጓዣ መስመር ሙሉ በሙሉ ሊዘጋ ይችላል። ይህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ክፉኛ እንዲዳከም ሲያደርገው፥በሌላ በኩል ሶማሊያ እንደገና ወደ የባህር ወንበዴዎች(Pirates )ዘመን እንድትመለስ ያደርጋታል። በዚህ ሁኔታ አሜሪካ በሶማሊያ ወይም በየመን ላይ ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ ትችላለች።
ሁኔታ ሶስት፡ የኢራን ውድቀት እና አዲስ የኃይል ሚዛን
የኢራን ስርዓት በዚህ ጦርነት ምክንያት ከውስጥም ሆነ ከውጭ ከባድ ጫና ከገጠመው እና ውድቀት ከተፈጠረ፣አፍሪካ ቀንድ አዲስ የጂኦፖለቲካል ክስተት ውስጥ ሊገባ ይችላል።በዚህ ሁኔታ የሂውቲዎች የጦር መሳሪያ አቅርቦት ይቋረጣል። ይህ ደግሞ ሳውዲ አረቢያ እና ኤሚሬትስ በየመን ያላቸውን ጦርነት ለመቋጨት እድል ይሰጣቸዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በሱዳን ውስጥ በኢራን የሚደገፉ ኃይሎች ደካማ ስለሚሆኑ፣ የሱዳን ጦር እና RSF መካከል ያለው ሚዛን ሊለወጥ ይችላል። ለኢትዮጵያ ደግሞ የቀይ ባህር መዳረሻ ጥያቄ አዲስ እድል ሊከፍትላት ይችላል።


